አሜሪካ፡ የካንሰር ታማሚው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ በሎተሪ አሸነፉ

ሎተሪ የሚፍቅ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካዋ ሰሜን ካሮላይና አንድ ግለሰብ ለካንሰር ኬሞቴራፒ ህክምና ለማድረግ እግረ መንገዳቸውን የገዙት የሎተሪ ቲኬት የ200 ሺ ዶላር (5.9 ሚሊየን ብር) አሸናፊ አድርጓቸዋል።

ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ ግለሰቡ የመጨረሻ የኬሞቴራፒ ህክምናቸውን ለማድረግ በሚሄዱበት ወቅት ነበር ቲኬቱን የገዙት።

ሮኒ ፎስተር ለረጅም ዓመታት በአንጀት ካንሰር በሽታ ሲሰቃዩ የነበረ ሲሆን መጀመሪያ በገዙት የሎተሪ ቲኬት አምስት ዶላር ካሸነፉ በኋላ በአምስት ዶላሩ ተጨማሪ ሁለት ቲኬቶችን ገዝተዋል።

ከሁለቱ ቲኬቶች መካከል አንደኛው ምንም አልነበረውም፤ ሁለተኛው ግን ያልጠበቁትን እድል ይዞ ነበር።

'' ሁለተኛውን ትኬት ስፍቀው በጣም ብዙ ዜሮዎችን ተመለከትኩ፤ ማማን አቅቶኝ ቆሜ ቀረሁ'' ብለዋል። ሮኒ ፎስተር አክለውም ከሎተሪው ካገኙት ገንዘብ መካከል ጥቂቱን የህክምና ወጪያቸውን ለመሸፈን እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል።

ለሰሜናዊ ካሮላይና ትምህርታዊ ሎተሪ ድርጅት አስተያየታቸውን የሰጡት የሎተሪው አሸናፊ '' ሎተሪው ከመድረሱ በፊት እራሱ የመጨረሻ ዙር የኬሞቴራፒ ህክምናዬን ላደርግ ስለነበር በጣም ደስተኛ ነበርኩ'' ብለዋል።

'' ሎተሪ ማሸነፌ ደግሞ ይበልጥ ቀኔን አሳመረው።'' ብለዋል።

ሮኒ ፎስተር ከግብር በኋላ 141 ሺ ዶላር ወይም 4.2 ሚሊየን ዶላር የሚያገኙ ይሆናል።በትራንስፖርት ቢሮ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩት ግለሰቡ በአሁኑ ሰአት ጡረታ ወጥተው ነው የሚገኙት።

ምንም እንኳን የጤና መድህን ሽፋን ቢኖረኝም የካንሰር ህክምና ተጨማሪ ብዙ ወጪዎች ስላሉት ካገኘሁት ገንዘብ መካካል ጥቂቱን ለህክምናዬ ለማዋል ወስኛለው ሲሉ በደስታ ተውጠው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።