"በኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊ ግድያ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለ የለም" የነቀምቴ ፖሊስ አዛዥ

ገመቺስ ታደሰ

የፎቶው ባለመብት, FB irraa

የኢትዮ ቴሌኮም የምዕራብ ዞን ኃላፊ የነበሩት አቶ ገመቺስ ታደሰ ከትናንት በስቲያ ዕሁድ አመሻሽ 1 ሰዓት ገደማ ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የነቀምቴ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኮማንደር ግርማ አብዲሳ እስካሁን በግድያው ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው የለም ብለዋል።

በነቀምቴ ከተማ የደህንነት ስጋት የለም ያሉት ኮማንደር ግርማ የአቶ ገመቺስ ገዳዮችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የምርመራ ስራዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉ ተናግረዋል።

አቶ ገመቺስ ህይወታቸው ሳያልፍ ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆዩ ህይታቸው ማለፉን የነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዳምጠው ጋረደው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሜዲካል ዳይሬክተሩ አቶ ገመቺስ ቢያንስ አራት ጊዜ በጥይት መመታታቸውን እና አንድ ጊዜ ደግሞ በስለት መወጋታቸውን ያረጋግጣሉ።

"ግራ እጁ ላይ ሁለት ጊዜ በጥይት ተመቷል። ትከሻው ላይም በጥይት ተመቶ በብብቱ በስተግራ በኩል ጥይቱ ወጥቷል" ያሉ ሲሆን፤ እግሩ ታፋው አካባቢ ሁለት ቦታ መመታቱን እና ጥይቶቹ የገቡበት እና የወጡበት ቦታ እንደሚታይ ይናገራሉ።

ዶ/ር ዳምጠው እንደሚሉት ከሆነ የአቶ ገመቺስ ህይወት በፍጥነት እንዲያልፍ ያደረገው ደረታቸው ላይ በስለት መወጋታቸው ነው።

የፎቶው ባለመብት, Facebook

"ደረቱ ላይ በስለት ተወግቷል። በስለት የተወጋበት ቦታ በጣም ሰፊ። ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገውም ይህ ነው። እኔ ሆስፒታል ነበርኩ። ሲመጣ በህይወት ነበር ግን ብዙ ደም ፈሶት ስለነበር ህይወቱን ማትረፍ አልተቻለም" በማለት የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

አቶ ገመቺስ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በማናጅመንት የዶክትሬት ድግሪያቸውን እየተማሩ ነበር።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲም በአቶ ገመቺስ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ለዓመታት አንድ ዶርም መጋራታቸውን እና ከወራት በፊት ስለተሞከረበት ግድያም አነጋግሮት እንደነበር ሄኖክ የተባለ የአቶ ገመቺስ ጓደኛ በትዊተር ገፁ አስፍሯል።

ሄኖክ እንዳለው ገመቺስ ጥሩ ውጤት ከነበራቸው ተማሪዎች መካከል ነበር። በጅማ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ የገመቺስ ፍላጎት እንደ ብዙዎቻቸው ወደ ውጭ ሃገር መሄድን ወይም አዲስ አበባ ላይ ስመ ጥር ኩባንያዎችን መቀላቀል አልነበረም። ይልቁንም ወደ ነቀምት መመለስ ነበር።

ከወራት በፊት የግድያ ሙከራ ተደረገበት የሚል መረጃ ሰምቶም ገመቺስን ጠይቆት እንደነበር እና ለዚህም ገመቺስ የሰጠውን ምላሽ ጭምር ሄኖክ ፎቶ አንስቶ በትዊተር ገፁ አውጥቶታል።