ኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ሁከት 359 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ከፍያለው ተፈራ
የምስሉ መግለጫ,

ከፍያለው ተፈራ

ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል አጋጥሞ ከነበረው ግጭትና ጥቃት ጋር በተያያዘ 359 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ያለው ሁኔታ እየተረጋጋ መምጣቱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ከፍያለው ተፈራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።ኮሚሽነር ጀነራሉ እሁድ ዕለት የሟቾች ቁጥር 67 እንደሆነ መናገራቸውን አስታውሰው፤ ከዚያ ወዲህ በግጭት ሳቢያ የሞቱ ሰዎች አለመኖራቸውን ገልጸዋል።

በአብያተ ክርስቲያኖቿና በምዕመኖቿ ላይ ጥቃት እንደተፈጸመ የገለጸችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሕዝብ ግነኙት ኃላፊ የሆኑት መልዓከህይወት አባ ወልደየሱስ ሰይፉ በበኩላቸው 60 የሚደርሱ የእምነቱ ተከታዮች ባለፈው ሳምንት ባጋጠመው ሁከት መገደላቸውን ተናግረዋል። አክለውም "ከእሁድ ወዲህ በሞጆ ከተማ 1 ሰው በባሌ ሮቤ ደግሞ 2 ሰዎች ተገድለው ተገኝተዋል። የሰዎቹ ግድያ ከግጭቱ ጋር የተያያዘ ይሁን በሌላ ምክንያት ይሁን አስካሁን አልታወቀም። የማጣራት ሥራዎች እየተሰሩ ነው" ሲሉ አመልክተዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ከፍያለው ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች 80 በመቶ (54 ሰዎች) የሞቱት በእርስ በእርስ ግጭት እንደሆነ እና የተቀሩት ደግሞ ከጸጥታ አስከባሪ ጋር በነበረው ግጭት ህይወታቸውን ያጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ከተቃውሞ ሰልፍ ወደ ሃይማኖታዊ መልክ ወደላው ግጭት በተቀየረው ሁከት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት 'ይሄኛው አካል ነው ወይም ያኛው ነው' ማለት አይቻልም ብለዋል ኮሚሽነሩ።

"ሁከቱ ወደ ሃይማኖታዊ ግጭት ከተቀየረ በኋላ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የዚኛው ሃይማኖት ተከታይ ነው ማለት አይቻልም። የተቃውሞ ሰልፉ ወደ ግጭት ከተቀየረ በኋላ በሁለቱም ጎራ ባሉት ሃይማኖት ተከታዮች በኩል ህይወት ጠፍቷል" ብለዋል።

የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሞቱብኝ ምዕመኖች ቁጥር 60 ነው ማለቷን ተከትሎ ኮሚሽነር ጀነራል ከፍያለው በሰጡት ምላሽ "እኛ እንዲህ አይነት መረጃ የለንም። በክልሉ ውስጥ የሚፈጠረውን የምንቆጣጠረው እኛ ነን። እነሱ ይህን መሰል መረጃ ከየት እንዳመጡ አናውቅም" ብለዋል።

የፖሊስ ኮሚሽነሩ ጨምረው እንደተናገሩት ሰሞኑነ በነበረው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው ሦስት የዕምነት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

"በአዳማ ከተማ አንድ መስጅድ እንዲቃጠል ተደርጓል። ከአዳማ ወጣ ብለው በሚገኙ ገጠራማ ስፍራዎች ደግሞ አንድ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን እና ሌላ አንድ ግንባታው ገና እየተጀመረ ያለ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተቃጥሏል" ብለዋል።

ከሰሞኑ የተከሰተውን ግጭት ኦሮሚያ ፖሊስ ፈጥኖ መቆጣጠር ላይ ድክመት አሰይቷል በሚባለው ትችት ላይ ምላሻቸውን ሲሰጡ "የኦሮሚያ ፖሊስ ግጭቱን ለመቆጣጠር ህይወት እስከመክፈል ድረስ መስዋትነት እየከፈለ ነው" ነው በማለት የክልሉ ፖሊስ ጥረት ማድረጉን አመልክተዋል።

በሁሉም ስፍራዎች የወጡት የተቃውሞ ሰልፎች ከአቅም በላይ የሆኑ እንደነበሩ የጠቀሱት የፖሊስ ኮሚሽነሩ፤ ከሌሎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ግጭቱ አሁን ወደ ደረሰበት ደረጃ እንዲወርድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው የኦሮሚያ ፖሊስ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ከፍያለው ተፈራ በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት በተተኮሰ ጥይት ሰዎች መገደላቸውንም አምነዋል።

"በአምቦ ከተማ ይህን መሰል ክስተት አጋጥሟል። ይህን ድርጊት የፈጸሙትም በአስቸኳይ በቁጥጥር ሥር ውለው የምረመራ እየተከናወነባቸው ነው። የወሰዱት እርምጃ ተመጣጣኝ ነው ወይ? ይህን እርምጃ እንዲወስዱ ያስገደዳቸው ሁኔታ ምን ነበር? የሚሉት ጉዳዮች ከተመረመሩ በኋላ መጠየቅ ያለበት ሰው ተጠያቂ ይደረጋሉ" ብለዋል።

'ኦሮሚያ ፖሊስ ለአንድ አካል ወግኗል'

ኦሮሚያ ፖሊስ ለአንድ አካል ወግኗል የሚለውን ክስ ኮሚሽነር ጀነራሉ አይቀበሉትም። "ይህ አይነት ባህሪም በአባላቶቻችን ዘንድ አልተስተዋለም" ብለዋል። "ፖሊሶቻን ሁሉንም ህዝብን ይታደጋሉ። በሁከቱ ወቅት በሁለቱም ጎራ የነበረውን ከግንዛቤ በማስገባት የሕግ ማስከበር ሥራውን ሲያከናውን ነበር። ለአንድ ወገን አድልቶ ሌላውን ሲጎዳ ነበር የሚለው ፍጹም ውሸት ነው" ብለዋል ኮሚሽነር ጀነራሉ።

ባለፈው ሳምንት ካጋጠመው አለመረጋጋት ጋር ግነኙነት አላቸው ተብለው በመጠርጠር በቁጥጥር ስር ከዋሉት 359 ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችንም በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተረሰራ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽንር ከፍያለው፤ አሁን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ችግሩ ተፈጥሮባቸው የነበሩት ከተሞች ወደ ቀደመ ሰላማቸው ተመልሰዋል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ ጨምረውም "አሁን ላይ የተዘጉ መንገዶች የሉም፣ ሰው ወደ ዕለት ሥራው ተሰማርቶ በሰላም እየመሰል ነው፣ በሁከቱ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው ቤቶች መልሰው እየተገነቡ ነው፣ በተለየዩ ከተሞችም ከህዝብ ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ረቡዕ በኦሮሚያ፣ በድሬዳዋና ሐረር ውስጥ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ባጋጠሙ ግጭቶችና ጥቃቶች ሳቢያ ከ65 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንዳጋጠመ ተነግሯል።

ከዚህ በተጨማሪም የእምነት ቤቶች፣ የንግድ መደብሮች፣ መኖሪያ ቤቶችና ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች በእሳት ቃጠሎ የመውደምና ከጥቅም ውጪ የመሆን ጉዳት ደርሶባቸዋል።