የሠርጋቸው ቀን ምሽት ለትዳራቸው መፍረስ ምክንያት የሆነባቸው ሴቶች

ሙሽራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሠርግ በየትኛውም የዓለም ክፍል አስደሳች አጋጣሚ ቢሆንም የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ከባድ የሥነ ልቦና ስብራት የሚያስከትሉ የሚሆኑባቸው የዓለም ክፍሎችም አይታጡም።

በበርካታ የአረቡ አገራት ሴቶች ሲያገቡ ክብረ ንጽህናቸውን እንደጠበቁ እንዲሆኑ ይጠበቃል። የሠርጋቸው ዕለት ቀሪ ህይወታቸውን ሲኦል ያደረገባቸው ሴቶች የህይወት ልምዳቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

የ23 ዓመቷ ሶማያ

ትወደው የነበረው ፍቅረኛዋን እንድታገባ ስላልፈቀዱላት ከቤተሰቦቿ ጋር ትልቅ ግጭት ውስጥ ገብታ ነበር። ሶሪያዊቷ ሶማያ በደማስቆ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ጽሁፍ ዲግሪዋን ለማግኘት ትምህርቷን ወደ ማጠናቀቁ ነበረች። ምንም እንኳ ቤተሰቦቿ ፍቅረኛዋ ኢብራሂምን እንዳታገባው ቢከለክሏትም ልታገባው ወሰነች።

የሠርጋቸው ዕለት ምሽት ግን ፍቅር የሚባል ነገር በመካከላቸው እንደነበር እስክትጠራጠር ድረስ ነገሮች ወደ መጥፎ ተቀየሩ።

የሠርጋቸው ዕለት ምሽት ወደ መኝታቸው ሲሄዱ ፍቅረኛዋ እና ባሏ ኢብራሂም እሷ ምን እየተሰማት እንደሆነ ለማወቅ ግድም ሳይሰጠው ወሲብ እንዲፈፅሙ አደረገ።

ሶማያ በዝምታ የሚፈልገውን እንዲያደረግ ከመፍቀድ ባለፈ ልትታገለው አልሞከረችም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንሶላ ላይ ምንም ዓይነት ደም ባለማየቱ ኢብራሂም በጥርጣሬ ተመለከታት። ጥርጣሬው ገብቷት ነገሩን ለማብራራት ሞከረች።

ብዙ ሴቶች ድንግልናቸው ሲገሰስ የሚደሙ ቢሆንም የማይደሙ እንዳሉም የህክምና ባለሙያዎች ያረጋግጣሉ።

ሃኪሞች እንደሚሉት ነገሩ ከሴት ሴት ሊለያይም ይችላል። ድንግልናቸው የግድ በቀዶ ህክምና እንዲሄድ የሚደረጉም ሲኖሩ ያለ ድንግልና የሚወለዱ ሴቶች እንዳሉ እንዲሁም ልጅ ሳሉ በሚደርስ ድንገተኛ ጉዳት ድንግልናቸውን የሚያጡም አሉ።

የሶማያ ማብራሪያ ለውጥ አላመጣም። "እንደ ጦር በሚወጉ አይኖቹ ተመለከተኝ። በዚህ አስተያየቱ ሳያውቀው እንደገደለኝ ነው የተሰማኝ" በማለት ያን አስደንጋጭ አጋጣሚ ትገልጻዋለች።

ሊያናግራት አልፈለገም ችሎት የቀረበ ተጠርጣሪ የመሆን ስሜት ተሰማት። አንዳቸው ስለ ሌላኛቸው ብዙ እንደሚያውቁ ያስቡ የነበረ ቢሆንም የድንግልና ምልክት ባለመታየቱ ሁሉም ነገር እንዳልነበር ሆነ።

'ደም የነካ አንሶላ' ለወንዶች ምናቸው ነው?

አያት ቅድመ አያቶቿ በዚህ ቢያልፉም ፍቅረኛዋ የተማረ ሰው በመሆኑ ራሷን እዚህ ቦታ ላይ አገኘዋለሁ ብላ አላሰበችም።

የተገሰሰ ድንግልናን በቀዶ ህክምና መመለስ እንደሚቻል የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። ባሏ ኢብራሂም በሠርጋቸው ማግስት ድንግል እንደነበች ለማረጋገጥ ወደ ዶክተር እንዲሄዱ ጠየቃት።

ምርመራ ያደረገላት የማህፀን ሃኪም ድንግልናዋ ወፍራም በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ሊገሰስ የሚችለው ስትወልድ ብቻ እንደሆነ ገለጸላቸው። ባሏ በእፎይታ ተንፍሶ በፈገግታ ተመለከታት። ግን ሶማያ ልትፈታው ወስናለችና ዘግይቶ ነበር።

"የተሰማኝን በቃላት መግለጽ አልችልም። የኔነቴን ዋጋ ወደ አንድ ድንግልና የሚባል ተራ ነገር ከቀነሰ ሰው ጋር ቀሪ ህይወቴን ልኖር አልችልም። እኔ ሰው እንጂ ቁራጭ ሥጋ አደለሁም" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አጋጣሚው ሶማያ ላይ ከባድ የሥነ ልቦና ጉዳት አድርሷል።

ድንግል ነን ካሏቸው ፍቅረኞች ጋር ወሲብ በፈጸሙ በመጀመሪያ ቀን ደም ባያዩ ምን እንደሚሰማቸው እድሜያቸው ከ20 - 45 የሚሆኑ 20 ወንዶችን ቢቢሲ አስተያየት ጠይቋል። ከእነዚህ ውስጥ ምሁራን፣ ዶክተሮችና መምህራን ይገኙበታል። በጥቅሉ ሰፊ ምልከታ አላቸው የሚባሉ ወንዶች ናቸው አስተያየት ሰጪዎቹ።

በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የብዙዎቹ መልስ ደም ማየታቸው ለቀጣዩ ፍቅርና የትዳር ህይወታቸው አስፈላጊ ምልክት ነው የሚል ነበር።

የ45 ዓመቷ ጁማናህ

በሶሪያዋ አሌፖ የኖረችው ጁማናህ ወደ ቤልጀም የሄደችው እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ነበር። የ19 ዓመት ወጣት ሳለች ነው አባቷ ለቅርብ ዘመዳቸው የዳሯት።

እንደ ብዙ ወግ አጥባቂ ማህበረሰብ ሁሉ በአካባቢያቸው በሠርግ ምሽት በሙሽሮች መኝታ ቤት ዙሪያ ሆኖ ድንግልና እስኪገሰስ መጠበቅ ባህል ነበር።

ዛሬም ድረስ በደማቅ ትውስታ የሚታያት ያ ምሽት ለጁማናህ የስቃይ ነበር። ባሌ ነገሩን ቶሎ ፈጽሞ ውጭ ለሚጠብቁት ዘመዶቻችን የምስራቹን ለማድረስ ተጣደፈ። ምንም ሊያናግረኝ አልፈለገም።

"እንደዚያ ያለ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ስብራት ውስጥ ሆኜ የባሌ ብቸኛ ጭንቀት ደም የነካው ጨርቅ የማየት ነበር" ስትል ታስታውሳለች።

"በዚያች ምሽት እኔ አልደማሁም ስለዚህ ባሌ ደምጹን አጥፍቶ ተቀመጠ። ዓይኑ ግን እንደ እሳት ገረፈኝ "የምትለው ጁማናህ ለአንድ ሰዓት ያህል በድንጋጤና በፍርሃት መናወጧን ትናገራለች። እስኪነጋ ለመጠበቅ ትዕግስት ያጡት ቤተሰቦቿ በዚያው የሠርጓ ዕለት ሌሊት ወደ ማህፀን ሃኪም ወሰዷት።

"አስታውሳለሁ ሃኪሙ እንደ አባት ነበር ያጽናናኝ"

ሳትፈልግ በቤተሰብ ተገዳ በአደባባይ ካዋረዳት ባሏ ጋር ለ20 ዓመታት ለመኖር ተደደች። በነዚህ ጊዜያት አራት ልጆችንም ወልዳለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ድንግልናን በቀዶ ህክምና መመለስ

ሮዛና ከዓምስት ዓመት እጮኛዋ ጋር ተለያይታለች።

ምንም እንኳ ከጋብቻ በፊት ወሲብ አልፈፅምም ብላ ብትቆይም ዞሮ ዞሮ መጋባታችን አይቀርም ለሚለው የእጮኛዋ ውትወታ በመጨረሻ እጅ ትሰጣለች። ቅርብ ግንኙነት ያላቸው የሁለቱ ቤተሰቦች ተቀያይመው ይራራቃሉ። ከዚያም ሮዛናና እጮኛዋ ይለያያሉ።

በአካባቢው ድንግል ሆኖ አለመገኘት የሞትና የሽረት ጉዳይ በመሆኑ ሮዛና ከባድ ችግር ውስጥ ወደቀች። በመጨረሻ በጓደኛዋ ምክር በቀዶ ህክምና ሰው ሰራሽ ድንግልና እንዲኖራት ለማድረግ ወሰነች።

"በዚያ ቀላል ቀዶ ህክምና ባይሆን ዛሬ በህይወት አልኖርም ነበር" ትላለች ሮዛና።