ቦይንግ ከተሳፋሪዎች ደህንነት ትርፉን አስቀድሟል ተባለ

የቦይንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ሴናተሮች ኩባንያው የተሳፋሪዎችን ደህንነት ከማረጋገጥ ይልቅ ትርፉን አስቀድሟል ሲሉ ቦይንግን የወነጀሉት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሙ ዴኒስ ሙለንበርግ ከሴኔቱ የንግድ ቋማ ኮሚቲ ፊት ቀርበው ነገሮቸን ባብራሩበት ወቅት ነው።

ሴናተሮቹ ኩባንያው ትርፉን ብቻ በማስላት ቦይንግን ቶሎ ወደ ስራ ለማስገባት መጣደፉ ከባድ ችግር ነበር ሲሉ ወቅሰዋል።

በአምስት ወር ልዩነት በደረሰው በላየን አየር መንገድና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላኖች አደጋ በጥቅሉ 346 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ሴናተሮቹም ለሁለቱም አደጋዎች ምክንያት የሆነውን የአውሮፕላኑን ችግር ቦይንግ ቀደም ሲልም ያውቅ ነበር የሚለው ላይም በግልፅ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል።

ሴናተር ሪቻርድ ብሉሜንዛል እንዳሉት ቦይንግ ይሁንታን አግኝቶ ቶሎ ወደ በረራ እንዲገባ ኩባንያው ነገሮችን በጥድፊያ አድርጓል ሲሉ ደምድመዋል።

ከአደጋው ምርመራ ጋር በተያያዘም ቦይንግ በተደጋጋሚ ሆን ብሎ መረጃዎችን ሲያሳስትና ሲዋሽ እንደነበርም ገልፀዋል።