የአል ሻባብ ታጣቂዎች በኬንያ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ፈጸሙ

ካርታ

የሶማሊያው እስላማዊ ቡድን አል ሻባብ በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ ውስጥ ዋጂር በተባለ አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተዘገበ።

የእስላማዊው ቡድን ታጣቂዎች ዋጂር በሚባለው አካባቢ ደቡባዊ ክፍል በሚገኘው ዳዳጃቡላ ተብሎ በሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት ዛሬ ረቡዕ ጠዋት ነው።

ታጣቂዎቹ በፖሊስ ጣቢያው ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት ከባድ መድፍና ላውቸር ጭምር ተጠቅመው እንደሆነ ተዘግቧል።

አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ስለጥቃቱ እንደተናገሩት እስላመዊ ቡድኑ ፖሊስ ጣቢያውን ኢላማ ያደረገው ሁለት አባላቱ በቁጥጥር ስር ሆነው ፖሊስ ጣቢያው ውስጥ በመገኘታቸው ነው።

ጥቃቱን ተከትሎ በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ውስጥ በፖሊስ ጣቢያው ታስረው የነበሩት ሁለቱ የአል ሻባብ አባላት የተገደሉ ሲሆን ሁለት የፖሊስ አባላትና አንድ የአካባቢው ታጣቂ ላይ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።