የቀድሞ የአንጎላ ፕሬዝዳንት ልጅ ከፓርላማ አባልነት ታገደች

የቀድሞ የአንጎላ ፕሬዝዳንት እና የአሁኑ ፕሬዝዳንት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአንጎላ ፓርላማ ለረጅም ዓመታት ሃገሪቱን የመሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሆዜ ኤደዋርዶ ዶሳንቶስ ሴት ልጅ ከፓርላማ አባልነቷ ማገዱን አስታውቋል።

የቀድሞ ፐሬዝዳንቱን ተክተው ወደ ስልጣን የመጡት ጆዋ ሎሬንሶ ደግሞ በሀገሪቱ ተፈጽሟል ያሉትን የሙስና እና ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ከስረ መሰረቱ ለማስወገድ እርምጃዬን ጀምሬያለው ብለዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ልጅ ዌልዊሺያ ዶሳንቶስ እ.አ.አ. በ 2008 ነበር የሃገሪቱ ፓርላማ አባል ተደርጋ የተመረጠችው። ነገር ግን ባለፈው ዓመት የአንጎላ የደህንነት አባላት ማስፈራሪያ እያደረሱብኝ ነው በማለት ወደ እንግሊዝ ሄዳለች።

ፓርላማው በበኩሉ ዌልዊሺያ በፓርላማው ስለማይገኙ ከአባልነታቸው ሰርዤያታለው ብሏል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ልጅ በሃገሪቱ የተፈራችና ከፍተኛ ተጽህኖ የነበራት ሴት ሰስትሆን መገናኛ ብዙሃንንም ጭምር ትቆጣጠር ነበር። እንደውም በሃገሪቱ ትልቅ የሚባል አንድ የማስታወቂያ ድርጅትን ታስተዳድርም ነበር።

እንግሊዝ በነረችበት ወቅት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የአሁኑን መሪ ጆዋ ሎሬንሶ ላይ ከፍተኛ ትችቶችን ትሰነዝር ነበር ተብሏል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሆዜ ኤደዋርዶ ዶሳንቶስ በነበራቸው የ 38 ዓመታት አገዛዝ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሃላፊነቶች ላይ በርካታ የቤተሰብ አባላቶቻቸውን ይሾሙ እንደነበር ይነገራል።

እ.አ.አ. በ 2017 ነበር ፕሬዝዳንቱ ስልጣናቸው ለቅቀው ለአሁኑ ፕሬዝዳንት ቦታውን ያስረከቡት።