በፓኪስታኑ የባቡር አደጋ 74 ሰዎች ህይወታቸው አለፈ

በእሳት የተቀጣጠለው ባቡር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በፓኪስታን ከካራቺ ወደ ራዋልፒንዲ ሲጓ የነበረ ባቡር ላይ ባጋጠመ የእሳት አደጋ የ74 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለፀ።

የፓኪስታን የባቡር መንገድ ሚኒስትር ሼክ ራሺድ አህመድ እንዳስታወቁ የእሳት አደጋው የደረሰው መንገደኞች ቁርስ ለማዘጋጀት ሲጠቀሙበት የነበረ የጋዝ ሲሊንደር በመፈንዳቱ ነው።

ፍንዳታውን ተከትሎ የተነሳው የእሳት ነበልባልም በትንሹ ሶስት የባቡሩ ፉርጎዎችን ማዳረሱንም ታውቋል።

የፓኪስታን መገናኛ ብዙሃን የአካባቢው ባለስልጣናትን ጠቅሰው እንደዘገቡት የአብዛኛው ተሳፋሪዎች ህይወት ሊያልፍ የቻለው ከእሳት አደጋው ለማምለጥ ከባቡሩ በመስኮት ለመዝለል ሲሞክሩ ነው።

በአደጋው ህይወታቸው ካጡት 74 ሰዎች በተጨማሪ 40 ሰዎች የተለያየ አይነት ጉዳት እንደደረሰባቸው ሚኒስትሩ አክለዋል። የሟቾችም ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።

በፓኪስታን ረጅም መንገድ የሚጓዙ ሰዎች ምግባቸውን በባቡር ላይ ለማብሰል ስቶቭ ይዘው እንደሚሳፈሩ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ይህ ትልቁ ችግር ነው ሲሉም ሁኔታውን አስረድተዋል።

በባቡሩ ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል የሱኒ ሙስሊም ንቅናቄ ባዘጋጀው ሃይማኖታዊ ኮንፍረንስ ላይ ለመሳተፍ ራይዊንድ ወደተባለች ከተማ ሲጓዙ የነበሩ ሰዎች በብዛት እንደሚገኙበት ታውቋል።

ባቡሩ ወደ ሌላ ቦታ ሊጓዝ የነበረ ቢሆንም ለሃይማኖታዊ ተጓዦቹ ተብሎ ነው አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ራይዊንድ እንዲሄድ የተደረገው።

የፎቶው ባለመብት, Rescue1122

በባቡሩ ላይ ተሳፍሮ የነበረውና በህይወት መትረፍ የቻለው ሞሀመድ ራምዛን ለመቢቢሲ ሲናገር '' አንዳንዶቹ ተሳፋሪዎች የጋዝ ሲሊንደር በመጠቀም ሻይ እያፈሉ እያለ ነው ድንገት የፈነዳው'' ብሏል። እሱ ከባቡሩ ዘሎ በመውጣት ነው ህይወቱን ማትረፍ የቻለው።

የግዛቱ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀሚል አህመድ ''በእሳት አደጋው ህይወታቸውን ካጡት መካከል አንዳንዶቹ ክፉኛ ከመቃጠላቸው የተነሳ ማንነታቸውን ለመለየት እንኳን አልተቻለም፤ ለዚህም የዘረ መል ምርመራ ማድረግ እንገደዳለን'' ብለዋል።

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ከሃን በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት በአደጋው ማዘናቸውን ገልፀው አስቸኳይ ምርመራ እንዲካሄድ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።