ተሰንጥቋል የተባለው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ከበረራ ታገደ

የአውስትራሊያው አየር መንግድ ካንታስ፤ ቦይንግ 737 ኤንጂን ውስጥ ስንጥቅ በማግኘቱ አውሮፕላኑን ከበረራ ማገዱን ይፋ አደረገ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአውስትራሊያው አየር መንግድ ካንታስ፤ ቦይንግ 737 ኤንጂ የተባለው አውሮፕላን ላይ በማግኘቱ አውሮፕላኑን ከበረራ ማገዱን ይፋ አደረገ።

ቦይንግ፤ የ737 ኤንጂ አውሮፕላኖች ክንፋቸው ሊሰነጠቅ እንደሚችል ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፤ በርካታ አየር መንገዶች አውሮፕላናቸውን እየፈተሹ ነው።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፤ በመላው ዓለም ወደ 50 የሚጠጉ አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደዋል።

ካንታስ አውሮፕላኑ ላይ የተገኘው ስንጥቅ አሁን ላይ ለአደጋ ባያጋልጥም፤ ደህንነታቸው አስተማማኝ ያልሆነ አውሮፕላኖችን ማብረር እንደማያስፈልግ ተናግሯል።

ቦይንግ የአውሮፕላኖቹን አካል ከክንፍ ጋር በሚያገናኘው ቦታ ላይ ስንጥቅ መገኘቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ባለፈው ወር የአሜሪካ የበረራ ተቆጣጣሪ ተቋም ከ30 ሺህ ጊዜ በላይ የበበሩ ቦይንግ 737 ኤንጂ አውሮፕላኖች ላይ ፍተሻ እንዲደረግ አዞ ነበር።

ካንታስ በበኩሉ ከ30 ሺህ ጊዜ በላይ የበረሩ ቦይንግ 737 ኤንጂ አውሮፕላኖች እንደሌሉት ገልጾ፤ ስንጥቅ ያገኘው ከ27 ሺህ ጊዜ በታች በረራ ባካሄዱ አውሮፕላኖች ላይ መሆኑን አሳውቋል።

ቦይንግ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኢንዶኔዥያ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ከበረራ መታገዳቸው ይታወሳል።

ቦይንግ 737 ኤንጂ አውሮፕላን ከቦይንግ 737 ማክስ ቀድሞ የተሠራ ነው።

የአሜሪካው አየር መንገድ ሳውዝዌስት ኤርላየንስ በቅርቡ በቦይንግ 737 ኤንጂ አውሮፕላኖቹ ላይ ስንጥቅ አግኝቶ እንደነበር ይታወሳል።