አይኤስ አል ባግዳዲን የሚተካውን አዲስ መሪ ይፋ አደረገ

አቡባካር አል ባግዳዲ

የፎቶው ባለመብት, Image copyrightUS DEPARTMENT OF DEFENSE/REUTERS

እስላማዊው ቡድን አይኤስ መስራቹና መሪው አቡባካር አል ባግዳዲ መገደሉን ለመጀመሪያ ጊዜ አረጋግጦ ቡድኑን በመምራት የሚተካውን ሰው ስም ይፋ አድርጓል።

የአይኤስ መልዕክት ማስተላለፊያ በሆነው የቴሌግራም መድረክ ላይ ቡድኑ እንዳስታወቀው አዲሱ መሪና "ካሊፋ" አቡ ኢብራሂም አል ሐሼሚ አል ቁራሺ መሆኑን ገልጿል።

የአሜሪካ ልዩ ኃይሎች ባለፈው እሁድ በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ውስጥ አል ባግዳዲ ያለበትን ካወቁ በኋላ ባካሄዱት ዘመቻ ነበር የአይኤስ መሪው እንደሞተ የተገለጸው።

አል ባግዳዲ የአሜሪካኖቹን ክትትል በመሸሽ ከመሬት በታች ወዳለ መተላለፊያ በመግባት ነበር የታጠቀውን ቦንብ አፈንድቶ ራሱን ያጠፋው።

ኢራቃዊው አልባግዳዲ አይኤስን መስርቶ ጥቃቶችን በማድረስ እውቅናን ካገኘበት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ አሜሪካና አጋሮቿ ያለበትን ለጠቆመ 25 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ለማበርከት ቃል ገብተው ሲፈልጉት ቆይተው ነበር።

አይኤስ ሐሙስ ዕለት የቃል አቀባዩ አቡ አል ሐሰን አል ሙሐጂርን ሞት አረጋግጧል። የሳኡዲ አረቢያ ዜጋና አልባግዳዲን ሊተካ ይችላል ተብሎ ይታሰብ የነበረው አል ሙሐጂር በሰሜናዊ ሶሪያ በአሜሪካና በሶሪያ የኩርድ ኃይሎች በተካሄደውና አል ባግዳዲን ኢላማ ካደረገው ጥቃት ከሰዓታት በኋላ ነበር የተገደለው።

አዲሱ የአይኤስ ቃል አቀባይ አቡ ሐምዛ አል ቁራሺ፤ ሁሉም ሙስሊሞች ለአዲሱ የአይኤስ መሪ አቡ ኢብራሂም አል ሐሼሚ ታማኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርቧል።

የአል ባግዳዲ ምትክ እንደሆነ የተነገረው የሐሼሚ ስም በደህንነት ተቋማት የማይታወቅ ሲሆን፤ ምናልባትም በቡድኑ ውስጥ ያለው መለያው ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።

አይኤስ ስለአዲሱ መሪው ሐሼሚ ዝርዝር መረጃንም ሆነ ማንነቱን የሚያሳይ ፎቶም ይፋ አላደረገም። ነገር ግን "በጂሃዳዊ እንቅስቃሴው ውስጥ ዋነኛ ሰው" እንደሆነ ተገልጿል።

ከቡድኑ በወጣው መግለጫ፤ ሐሼሚ ቀደም ሲል አሜሪካንን በመዋጋት ልምድ ያለው የጂሃድ ተዋጊ እንደሆነ ተገልጿል።