የስፔኑ ፍርድ ቤት ኃይል አልተጠቀሙም ያላቸውን 5 አስገድዶ ደፋሪዎች ነፃ አለ

ለ14 ዓመቷ ተጠቂ ተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የስፔኗ ባርሴሎና ፍርድ ቤት የ14 ዓመት ታዳጊ ላይ ፆታዊ ጥቃት በመፈፀም ተጠርጥረው እስር ላይ የነበሩ 5 ወንድ ልጆችን "ድርጊቱን ለመፈፀም ኃይል አልተጠቀሙም" ሲል በነፃ ማሰናበቱ በከተማዋ ተቃውሞ ቀስቅሷል።

ስለዚህ ታዳጊዎቹ በአስገድዶ መድፈር ሳይሆን በዝቅተኛ የፆታዊ ጥቃት ወንጀል የሚጠየቁ ይሆናል።

በስፔን ሕግ ፆታዊ ጥቃት አስገድዶ መድፈር የሚሆነው ኃይልን በመጠቀም ወይም በማስፈራራት ሲፈፀም ነው።

የስፔን መንግሥት በአሁኑ ወቅት ይህን ሕግ ለማሻሻል እየሠራ ነው።

ከዚህ በመነሳት የ14 ዓመቷ ታዳጊ ሰክራ ሯሷን ታውቅ ስላልነበር ወንዶቹ እሷ ላይ ፆታዊ ጥቃት ለመፈፀም ኃይል አልተጠቀሙም በሚል ነው ከአስገድዶ መደፈር ክስ ነፃ ያላቸው ፍርድ ቤቱ።

ቀደም ሲልም በዚህ ክስ መዝገብ ተመሳሳይ ውሳኔ ተላልፎ የነበረ ቢሆንም የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ሽሮት ነበር።

አሁን ደግሞ የባርሴሎናው ፍርድ ቤት የቀደመውን ውሳኔ አፅንቶ ታዳጊዎቹን ከአስገድዶ መድፈር ክስ ነፃ ብሏቸዋል።

መጀመሪያ ላይ በዚህ የክስ መዝገብ 6 ሰዎች ተከሰው 5ቱ ጥፋተኛ ተብለው ከአስር እስከ አስራ ሁለት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው ነበር።

በመጨረሻ ግን ፍርድ ቤቱ ተጠቂዋ በወቅቱ ምን እንዳደረገችና እንዳላደረገች አታውቅም፤ በነገሩ ለመስማማት ላለመስማማትም የምትችልበት አዕምሯዊ ብቃት አልነበራትም ብሏል። በዚህ ምክንያት ግለሰቦቹ ኃይልን ሳይጠቀሙ ወሲብ መፈፀም ችለዋል ብሏል።

ስለዚህም ለተፈፀመባት "በጣም መጥፎ ዓይነት ጥቃት" ካሳ ለተጠቂዋ አስር ሺህ ፓውንድ እንዲሰጣት ውስኗል።