ቻይና ጌም በሚያዘወትሩ ታዳጊዎች ላይ ሰዓት እላፊ ጣለች

ቻይና ታዳጊ 'ጌመኞች' ላይ ሰዓት እላፊ ጣለች Image copyright Getty Images

ቻይና በይነ-መረብ ላይ ተተክለው 'የቪድዮ ጌም' ሲጫወቱ የሚውሉ ታዳጊዎች ላይ እግድ ጥላለች።

ከ18 ዓመት በታች ያሉ 'ኦንላይን ጌመኞች' ከዚህ በኋላ ከምሽቱ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ ጠዋት ሁለት ሰዓት ድረስ መጫወት አይችሉም ተብሏል። አልፎም በሥራ ቀናት 90 ደቂቃ፤ ቅዳሜ እና እሁድ ደግሞ ለ3 ሰዓታት ነው መጫወት የሚፈቀድላቸው።

የቻይና ባለሥልጣናት፤ የበይነ-መረብ ቪድዮ ጌሞች ሱስ እየሆኑ ነው፤ ትውልዱንም ጤና እየነሱት ነው በሚል ነው ይህን ሕግ ያወጡት።

የወላጆች ራስ ምታት እየሆነ የመጣው የልጆች የጌም ሱስ

ቻይና የበይነ-መረብ ጨዋታ (የኦንላይን ጌሚንግ) ገበያ የደራባት ሃገር ናት። በዚህ ገበያ ከአሜሪካ በመቀጠል ከዓለም ሁለተኛ ተብላም ትቆጠራለች። ቻይና ሕግ በማብዛቷ ነው እንጂ ከዓለም ከፍተኛውን ድርሻ ለመያዝ ትችል እንደነበር ይነገርላታል።

በአዲሱ ሕግ መሠረት ዕድሜያቸው ከ8 እስከ 16 የሆኑ ታዳጊዎች ለጨዋታ በወር ማውጣት የሚችሉት 200 ዩዋን ነው። 860 ብር ገደማ መሆኑ ነው። ከ16 እስከ 18 ያሉ ደግሞ 400 ዩዋን (1600 ብር በላይ) ማውጣት ይችላሉ።

የቻይና መንግሥት የበይነ-መረብ ጨዋታን የሚቆጣጠር መሥሪያ ቤት ያቋቋመው አምና ነበር። ይህ ተቋም 'ስክሪን' ላይ ተሰክተው የሚውሉ ሕፃናትና ታዳጊዎችን ቁጥር የመቀነስ ኃላፊነት አለበት።

ለፌስቡክ ሱሰኞች የተገነባው አስፋልት ተመረቀ

አልፎም ቻይና ውስጥ አዲስ የቪድዮ ጨዋታዎችን ማስተዋወቅ እጅግ የከበደ እየሆነ ነው።

ባለፈው ዓመት የዓለም የጤና ድርጅት የቪድዮ ጨዋታዎች ሱስ እንደሚያስዙ ደርሼበታለሁ፤ የአዕምሮ ጤና ችግርም ሊያመጡ ይችላሉ ሲል ማወጁ አይዘነጋም።

የአሜሪካ የሥነ አዕምሮ ህክምና ማህበር የቪድዮ ጨዋታዎች የአዕምሮ ጠና መቃወስ ያመጣሉ ባይልም ሰበብ ሊሆን ስለሚችል ጥናት ያስፈልገዋል ይላል። ይህንን ተከትሎ አንዳንድ ሃገራት 'ቪድዯ ጌም' ክትትል ያሻዋል እያሉ ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ