ፈረንሳይ 1,600 ስደተኞችን ከጊዜያዊ መጠለያ አስወጣች

የፈረንሳይ ፖሊስ በሰሜን ፓሪስ ከሚገኙ ሁለት የስደተኛ መጠለያዎች 1,600 ስደተኞችን አስወጣ። Image copyright AFP

የፈረንሳይ ፖሊስ በሰሜን ፓሪስ ከሚገኙ ሁለት ጊዜያዊ የስደተኛ መጠለያዎች 1,600 ስደተኞችን አስወጣ።

600 የሚደርሱት ፖሊሶች ስደተኞቹን ፓሪስ ውስጥ ወዳለ ማዕከል የወሰዷቸው፤ የአገሪቱ መንግሥት ስደትን የሚገታ እርምጃ እንደሚወስድ ማሳወቁን ተከትሎ ነው።

አብዛኞቹ ስደተኞች ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራትና ከአፍጋኒስታን የመጡ ናቸው።

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ኑሮ በደዳብ

ስደተኞች በየዓመቱ 8 ቢሊዮን ዶላር ለቤተሰቦቻቸው ይልካሉ

በፓሪስ የቀለበት መንገድ አቅራቢያ የሚገኙት ሁለቱ ጊዜያዊ መጠለያዎች የተሠሩት ከፕላስቲክ ዳስ ነው። በመጠለያው ከሚኖሩ አንዷ የ32 ዓመቷ አይቮሪ ኮስታዊ አዋ እንደምትለው፤ ለአንድ ዓመት በመጠለያው ቆይታለች።

"ዳሱ ይቀዘቅዛል፤ ይዘንብብናልም። ከዚህ ተነስቼ የት እንደምሄድ ባላውቅም ጣሪያ ወዳለው ሥፍራ እንደምወሰድ ስለማምን ደስ ብሎኛል" ስትል ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግራለች።

Image copyright AFP

ስደተኞች በየቦታው ጊዜያዊ መጠለያ እንዳይሠሩ 16 ሺህ ሰዎችን የሚይዙ ሦስት አዳዲስ የስደተኞች መጠለያዎች እንደሚቋቋሙ የፈርናሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ክሪስቶፈር ካስትነር አስታውቀዋል።

ጥገኝነት የጠየቁና ያገኙ ስደተኞች እንዲሁም ጥገኝነት የተከለከሉ ስደተኞችም ጉዳይ በቅርበት እንደሚታይም አክለዋል።

በርካታ የአውሮፓ አገሮች የስደተኞች ፖሊሲያቸውን እያጠነከሩ መጥተዋል። ፈረንሳይም ተመሳሳይ እርምጃ እንድትወስድ ጫና ተደርጓል።

በሊቢያ የባህር ዳርቻ ስደተኞች ሰጠሙ

የመጀመሪያ ዙር ስደተኞች ሊቢያን ለቀው ሩዋንዳ ገቡ

ፈረንሳይ ከአውሮፓ ውጪ ከሚገኙ አገሮች የሚመጡ ሠራተኞችን ቁጥር እንደምትገድብ ባለፈው ረቡዕ ይፋ አድርጋለች። አገሪቱ ውስጥ ለመኖር ፈቃድ የሌላቸው የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ እንደሚደረግም ተገልጿል።

በሰሜን ምሥራቃዊ ፓሪስ ከዳስ የተሠሩ ጊዜያዊ መጠለያዎች በዚህ ዓመት መጨረሻ እንደሚፈርሱም ይፋ ተደርጓል።

ተያያዥ ርዕሶች