የአይኤስና የአልሻባብ አባላት ፑንትላንድ ውስጥ ተረሸኑ

የሶማሊያ ካርታ

የእስላማዊዎቹ ቡድኖች የአልሻባብ እና በሶማሊያ ውስጥ የአይኤስ አባላት ሆነው ተገኝተዋል የተባሉ አምስት ሰዎች በሶማሊያዋ ከፊል ራስ ገዝ ክልል ፑንትላንድ ውስጥ በተኳሽ ቡድን መረሸናቸው ተነገረ።

ቦሳሶ ተብላ በምትጠራ ከተማ ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች ባካሄዱት ዘመቻ በቁጥጥር ስር የዋሉት እነዚህ አምስት ሰዎች ላይ በአካባቢው የሚገኝ አንድ ወታደራዊ ፍርድ ነው የሞት ቅጣት የበየነባቸው።

የእስላማዊ ቡድኖቹ አባላት ናቸው የተባሉት ሰዎችን ለመያዝ ዘመቻ የተካሄደው ከሁለት ዓመታት በፊት እስላማዊ ታጣቂዎች በክልሉ ውስጥ በሚገኝ ወታደራዊ ሰፈር ላይ ከባድ ጥቃት ከፈጸሙና አፍ-ኡሩር በሚባል መንደር ውስጥ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከገደሉ በኋላ ነው።

የአል ሻባብ ታጣቂዎች በኬንያ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ፈጸሙ

ብዙ ባሎችን አግብታለች የተባለች ሴት በአልሻባብ ተገደለች

የሞት ቅጣቱ የተፈጸመባቸው አምስቱ ሰዎች እድሜያቸው በ19 እና በ39 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውም ተነግሯል።

አዊል አህመድ ፋራህ የተባሉት የአካባቢው ወታደራዊ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደተናገሩት ፍርዱ ከተፈጸመባቸው ሰዎች መካከል አንዱ አንድ የፖሊስ መኮንን በመግደል የተጠረጠረ የአይኤስ ታጣቂ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌሎቹ አራት ሰዎች ለምን እንደተያዙ በተጠየቁበት ጊዜ ዳኛው ሲመልሱ "ላረጋግጥ የምፈልገው ነገር ቢኖር ሽብርተኛ መሆን . . . የሞት ቅጣት ማለት እንደሆነ ነው" ብለዋል።

አክለውም "የሞት ፍርዱ የተፈጸመባቸው ሰዎችም ሞቃዲሾ ውስጥ መዋጋታቸውንና ሰዎችን መግደላቸውን አምነዋል" በማለት "ስለዚህም ሞቃዲሾ ውስጥም ሆነ ቦሳሶ ውስጥ ሰውን መግደል ተመሳሳይ ነው" ብለዋል።

በተያያዘ ዜና ሌሎች አል ሻባብ አሚኒያድ የሚባለውና ግድያና የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶችን የሚፈጽመው የአል ሻባብ ክንፍ አባላት ናቸው የተባሉ አራት ሰዎች ደግሞ በተናጠል ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ውስጥ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ