ትራምፕ ህዳሴ ግድብ ሲያልቅ እመርቃለሁ ማለታቸው ተሰማ

የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ Image copyright Reuters

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ሚኒስትሮች የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ምርቃቱ ላይ በመገኘት ቀዩን ሪባን እቆርጣለሁ ማለታቸውን የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኃይል ሚኒስትር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ እንደገለፁት ትራምፕ ይህንን የተናገሩት በትናንትናው ዕለት አሜሪካ የሦስቱን አገራት ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድብ አሞላል እና ኦፕሬሽን ውይይት ከተሳተፉ በኋላ ነው።

በውይይቱ ላይ ከሦስቱ ሃገራት ሚንስትሮች ባሻገር የአሜሪካ የገንዘብ ሚንስትር እና የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ተሳታፊ ነበሩ።

ሦስቱ ሃገራት በዋሽንግተን ምን ተስማሙ?

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትን እንደማትቀበል አሳወቀች

ኢንጅነር ስለሺ በቀለ አክለው እንደገለፁትም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሦስቱ ሃገራት ከተውጣጡ ስድስት ልዑካን ጋር ተገናኝተው ጉዳዩንም ለመረዳት ሙከራ አድርገዋል ብለዋል።

ውይይቱም ካለቀ በኋላ፤ ግድቡ ከተጠናቀቀ በኋላ በምርቃቱ ላይ ሪባን መቁረጥ እንደሚፈልጉ እንደነገሯቸው ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንቱ ጨምረውም ልዩነቶቻቸውን አስወግደው ተባብረው እንዲሠሩ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል ብለዋል ሚኒስትሩ።

ከዚህም በተጨማሪ ለገንዘብ ሚኒስትራቸውም የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በተሳለጠ ሁኔታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚደረጉ ውይይቶች በተላሰለሰና ፈጣን ሁኔታ እንዲካሄዱ እንዲመሩ አቅጣጫ መስጠታቸውም ተገልጿል።

ከኢንጅነር ስመኘው ሞት በኋላ ህዳሴ ግድብ ምን ላይ ደረሰ?

አሜሪካ የአባይ ወንዝ አጠቃቀምን በተመለከተ መግለጫ አወጣች

ውይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ሦስቱን ሃገራት በመወከል የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ፕሬዚዳንቱ ግድቡን መመረቅ መፈለጋቸውን ምንም የጠቀሰው ጉዳይ የለም።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮቹ በየውሃ ሚንስትሮች ደረጃ የሚደረግ አራት መንግሥታዊ የቴክኒክ ስብሰባዎችን ለማካሄድ የተስማሙ ሲሆን፤ የዓለም ባንክ እና አሜሪካ ድጋፍ እንዲሰጡ እና በውይይቶቹ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን መግለጫው ያትታል።

በተጨማሪም ሚንስትሮቹ ጥር 6፣ 2012 ዓ.ም. ድረስ ከስምምነት ለመድረስ እንደሚሰሩ እና ኅዳር 29 እና ጥር 4 ዳግም በዋሽንግተን ለመገናኘት እና ሂደቱን ለመገምገም ቀጠሮ ይዘዋል።

እስከ ጥር 6፣ 2012 ዓ.ም. ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ በ2008 ተፈርሞ የነበረው የጋራ አቋም መግለጫ አንቀጽ 10 ተግባራዊ እንዲሆን ሚኒስትሮቹ ተስማምተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች