የአንበጣ ወረራ፡ የተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኤርትራና ሱዳንን አስጠነቀቀ

የበረሃ አንበጣ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የአንበጣ መንጋው በቀን በቶን የሚገመት እፅዋትን ያወድማል

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በቁጥጥር ሥር መዋል ካልተቻለ፤ ሰብል አውዳሚ የሆነው የአንበጣ መንጋ ጎረቤት አገራት ሊዛመት እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት በኢትዮጵያ አራት ክልሎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡን በመግለጫው አስታውሷል።

ከሶማሌላንድና የመን የመጣው አንበጣ በአምስት ክልሎች ተከስቷል

የአንበጣ መንጋው እስካሁን በሰብል ላይ ጉዳት አላደረሰም

መግለጫው አክሎም በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን ጠቅሶ እንደገለፀው አርሶ አደሮቹ በሰሜን አማራ አካባቢ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ጤፍና ሌሎች ሰብሎች ማጣታቸውን አትቷል።

ባሳለፍነው ሳምንት አንበጣው ወደ የተከሰተባቸው ቦታዎች የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ አውሮፕላን መላኩን መንግሥት አስታውቆ ነበር።

ይሁን እንጅ ወረራውን ለመከላካል የሚደረገው ጥረት ውጤታማ አለመሆኑ ተገልጿል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ከሆነ መንግሥት አንበጣውን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር ተግዳሮት ሆኖበታል።

"የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራውን ለመሥራት በአፋጣኝ ያለውን አቅምና ሐብት ተጠቅሞ ተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል" ሲሉ በፋኦ የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት ፋጡማ ሰይድ አሳስበዋል።

በአጠቃላይ የበረሃ አንበጣ መንጋው በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል በሰብል እና በግጦሽ ላይ ጉዳት አስከትሏል።

የአንበጣ መንጋው 350 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ በቀን 1.8 ሚሊየን ቶን እፅዋት ሲያወድም እንደነበር ፋኦ ግምቱን አስቀምጧል።

የመከላከል ሥራው ከተዳከመም አንበጣው በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዲሁም ወደ ሰሜን ምሥራቅ ኬንያ፣ የኤርትራን የተወሰኑ አካባቢዎች ፣ የሱዳን ደቡባዊ የባህር ዳርቻ ሊዛመት እንደሚችል ፋኦ አስጠንቅቋል።

የአንበጣ መንጋው ከሦስት ወራት በፊት ከየመን እንደመጣ ይነገራል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ