ዚምባብዌ 211 ሀኪሞችን ከሥራ አገደች

የዚምብብዌ ሀኪሞች ሰልፍ ሲያደርጉ Image copyright Getty Images

ዚምባብዌ ደሞዛችን አንሷል ብለው አድማ የመቱ 211 ሀኪሞችን አገደች።

የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ተቋም እንዳለው፤ ሀኪሞቹ መልቀቂያ ሳያስገቡ ለአምስት ቀናትና ከዚያም በላይ ሥራ አልገቡም።

ሀኪሞቹ የሥራ ማቆም አድማ የጀመሩት መስከረም ላይ ነበር።

በመንግሥት ሆስፒታሎች ከሚሠሩት 1,601 ሀኪሞች 516ቱ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ተገልጿል።

ዚምባብዌ በሺህ የሚቆጠሩ ነርሶችን አባረረች

"ሀኪሙ ትግሉን አቀጣጠለው እንጂ የሚታገለው ለታካሚው ነው"

የዚምባብዌ ሀኪሞች ስብስብ የሆነው 'ዚምባብዌ ሆስፒታል ዶክተርስ አሶሴሽን' ስለ መንግሥት እርምጃ እስካሁን ምንም አላለም። ከዚህ ቀደም ግን መንግሥት ሀኪሞች እያስፈራራ እንደሆነ ለሮይተርስ ገልጸው ነበር።

የሥራ ማቆም አድማ አገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ሆስፒታሎች ላይ ጫና አሳድሯል። በእነዚህ ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጠ ያለው የድንገተኛ አደጋ ክፍል ብቻ ነው።

"ማህበሩ የማያልፈው ቀይ መስመር የስራ ማቆም አድማ ነው"-ዶ/ር ገመቺስ ማሞ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት

የዚምባብዌ መንግሥት እንደሚለው ከሆነ ለሀኪሞች ደሞዝ የመጨመር አቅም የለውም። በተቃራኒው ሀኪሞቹ ያሉበትን ሁኔታ "ቀስ በቀስ የመሞት ያህል ነው" ሲሉ ይገልጻሉ። መንግሥት በአፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድም በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።

ዚምባብዌ ከፍተኛ የምጣኔ ኃብት ቀውስ ውስጥ ናት። የዋጋ ንረት የበርካቶችን ሕይወት ፈታኝ አድርጎታል።

ሀኪሞች በወር ከ100 ዶላር በታች ይከፈላቸዋል።

ዶ/ር ሊንዚ ሮበርትሰን "ደሞዛችን ለአስቤዛና ለቤት ኪራይም አይበቃም" በማለት የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ተያያዥ ርዕሶች