የዕድሜ ልክ እስረኛው ለአጭር ጊዜ "ሞቼ" ስለነበር ልለቀቅ አለ

እሰር ቤት Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ቤንጃሚን ሰው በመግደሉ ነበር እድሜ ልክ የተፈረደበት

አሜሪካ ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት የነበረ የዕድሜ ልክ እስረኛ ለአጭር ጊዜ "ሞቼ" ስለነበር ቅጣቴን ጨርሻለሁና ከእስር መለቀቅ አለብኝ በማለት ያቀረበው ጥያቄ በፍርድ ቤት ውድቅ ሆነ።

የ66 ዓመቱ አዛውንት ቤንጃሚን ሽሪቤር ያለ አመክሮ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት የተፈረደበት ከ23 ዓመት በፊት አይዋ ግዛት ውስጥ በፈጸመው የግድያ ወንጀል ነበር።

ታሳሪው ከእስር የመለቀቅ ጥያቄውን ያቀረበው ከአራት ዓመት በፊት ምንም እንኳን ሕይወቱ ብትተርፍም ባጋጠመው ድንገተኛ የጤና ችግር ምክንያት ልቡ ሥራውን አቁሞ ስለነበረ ነው።

የቤንጃሚንን ጥያቄ የተመለከቱት ዳኞች "የማያሳምን" ሲሉ ውድቅ አድርገውበታል።

ዳኞቹ አክለውም ቤንጃሚን ጥያቄውን ለማቅረብ ባመለከተበት ሰነድ ላይ ፊርማውን አኑሮ እያለ ሞቻለሁ ማለቱ "የማይመስል" ነገር ነው ብለዋል።

የፖለቲካ እስረኛ ማን ነው?

ተቃዋሚዎች የከንቲባዋን ጸጉር አስገድደው ላጩ

መብራት ማጥፋት የተከለከለው ዲፕሎማት

ከአራት ዓመት በፊት እስረኛው በኩላሊቱ ውስጥ በተፈጠረ ጠጠር ምክንያት ለሕይወቱ አስጊ የሆነ የጤና ችግር አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም ህክምና አግኝቶ ወደ እስር ቤቱ ሲመለስ ሙሉ ለሙሉ ድኖ ነበር።

ቤንጃሚን ባለፈው ዓመት ባቀረበው ነጻ የመለቀቅ ጥያቄው ላይ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ነፍስ እንዲዘራ የተደረገው ያለፍላጎቱ መሆኑን ጠቅሶ፤ በወቅቱ ለአጨር ጊዜ "በመሞቱ" ቀደም ሲል የተበየነበት የዕድሜ ልክ እስራት እዚያው ጋር ሊያበቃ ይገባል ሲል ጠይቆ ነበር።

ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ተመልክቶ ውድቅ በማድረጉ የእስረኛው ጠበቃ በጉዳዩ ላይ ይግባኝ ለመጠየቅ ከፍ ወዳለው የግዛቲቱ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው ገልጾ ነበር።

ነገር ግን ባለፈው ረቡዕ ፍርድ ቤቱ በህክምና ምርመራ እስረኛው መሞቱን የሚያረጋግጥ ውሳኔ እስካልተሰጠ ድረስ የእስረኛው ጥያቄ ተቀባይነት የለውም በሚል የበታች ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል።

ተያያዥ ርዕሶች