አሜሪካ በሱስ የተጠቁ ሰዎች ጭንቅላት ውስጥ መሣሪያ ልትተክል ነው

ኦፒዮድ በተባለው ህመም ማስታሻ ሱስ የወደቁ ታማሚዎች እንዲያገግሙ አዕምሯቸው ውስጥ መሣሪያ መትከል ሊጀመር ነው Image copyright WVU Medicine hospital

በአሜሪካ፤ ኦፒዮድ በተባለው ህመም ማስታሻ ሱስ የተጠመዱ ታማሚዎች እንዲያገግሙ አዕምሯቸው ውስጥ መሣሪያ መትከል ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ።

ጄሮድ ቡክሀተር የተባለው የ33 ዓመት ግለሰብ በኦፒዮድ ሱስ ከተያዘ ከአስር ዓመት በላይ ይሆነዋል። የአዕምሮ ቀዶ ጥገናው ከተደረገላቸው አንዱ ሲሆን፤ ዶ/ር አሊ ረዛይ እንዳሉት፤ አዕምሮው ውስጥ የተተከለው መሣሪያ "አዕምሮን የሚያረጋጋ ነው።"

በዚህ ወር መባቻ ላይ 'ዌስት ቨርጂንያ ዩኒቨርስቲ ሜዲካል ሆስፒታል' ውስጥ የተደረገውን ቀዶ ጥገና የመሩት ዶ/ር አሊ ረዛይ ነበሩ።

በቀዶ ጥገናው፤ የራስ ቅል በጠባቡ ተበስቶ ወደ አንድ ሚሊ ሜትር የሚድረስ መሣሪያ አዕምሮ ውስጥ ይከተታል። ይህም ሰዎች ራሳቸውን ከሱስ እንዲያቅቡ ይረዳል ተብሏል።

ፊደል ያልቆጠሩት ኢትዮጵያዊት የቀዶ ህክምና ባለሙያ

ቀዶ ህክምና በአፍሪካ ስጋት መሆኑ ከፍ ብሏል

ለቤተሰብ ምግብ ወይስ ለህክምና ይክፈሉ?

'ዲፕ ብሬን ስቲሙሌሽን' የተባለው ይህ መሣሪያ በአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት (ኤፍዲኤ) ፍቃድ አግኝቷል።

ከኦፒዮድ ሱስ ባሻገር፣ ለፓርኪንሰንስ፣ ለሚጥል በሽታና ሌሎችም ህክምና ሊውል እንደሚችልም እየተነገረ ነው።

ዶ/ር አሊ ረዛይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በተለያየ መንገድ ሱስን ለመከላከል ሞክረው ያልተሳካላቸው ሰዎች አዲሱን አማራጭ መጠቀም ይችላሉ።

ከመጠን በላይ ሱስ አስያዥ መድሀኒት መውሰድ፤ አሜሪካ ውስጥ ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎችን በመግደል ግንባር ቀደም ነው።

ዶክተሩ "ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህሙማን በተደጋጋሚ ወደ ሱስ ይመለሳሉ። አስጊ ችግር በመሆኑ መፍትሔ ልናበጅ ይገባል" ብለዋል።

የእንግሊዙ 'ሮያል ሶሳይቲ' በበኩሉ፤ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ ባዕድ መሣሪያ ማስገባት ላይ ጥያቄ አንስቷል። ፌስቡክና የኤለን መስክ ተቋም 'ኒውራሊንክ' ለማምረት ያሰቧቸው መሣሪያዎችን እንደ ማሳያ ይጠቅሳሉ።

ዶ/ር አሊ፤ እነዚህ የቴክኖሎጂ ተቋሞች በህክምናው ዘርፍ መግባታቸው ላይ የሚነሳው ጥያቄ እምብዛም አያሳምናቸውም።

"ስለ አዕምሮ የሚደረገው ጥናት በቴክኖሎጂ መደገፉ በጣም ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ" ሲሉ ያስረዳሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ