ኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዋጅ ልታጸድቅ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ Image copyright PM Office

የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 29/2012 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ እንዲጸድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መራ።

ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የሚፈጥረውን ችግር አሁን አገሪቱ ባሏት ሕጎች መፍታት የማይቻል በመሆኑ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቦ ነው ውይይት የተደረገበት ተብሏል።

“ኢትዮጵያ አዲስ የጥላቻ ንግግር ህግ አያስፈልጋትም” አቶ አብዱ አሊ ሂጂራ

ቴክቫህ ኢትዮጵያ፡ የፀረ ጥላቻ ንግግር የወጣቶች እንቅስቃሴ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት "የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለማህበራዊ ህይወት ስምረት፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፣ ለአገራዊ አንድነት፣ ለሰብዓዊ ክብር፣ ለብዝሃነት ጠንቅ መሆኑን" ጠቅሶ በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት መነጋገሩን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ማስተካከያዎችን በማድረግ ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

መግለጫው ጨምሮም "በተለይ በአሁኑ ወቅት በሕብረተሰቡ መካከል ያሉ መልካም እሴቶች በጥላቻ ንግግሮችና በሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸሩና ለአገርም ስጋት የደቀኑ መሆናቸውን" ጠቅሷል።

የጥላቻ ንግግርን የሚያሠራጩ ዳያስፖራዎች እንዴት በሕግ ሊጠየቁ ይችላሉ?

''ኢትዮጵያን ወደተሻለ ስፍራ ሊወስዳት የሚችል ሌላ መሪ የለም'' የሶማሌ ክልል ም/ፕሬዝዳንት

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በተመራው በዚህ መደበኛ ስብሰባው ላይ ከዚህ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ በተጨማሪም በሌሎች ረቂቅ ደንቦችና አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔን አሳልፏል።

ምክር ቤቱ የተመለከታቸው ሌሎች ጉዳዮች ደግሞ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ፣ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ፣ የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓትን ለመደንገግ በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ እና በኢትዮጵያና በጅቡቲ መንግሥታት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ለማስተላለፍ የተደረገውን ስምምነት ለማጽደቅ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ በዛሬው 75ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ በአጀንዳነት ይዞ የተመለከታቸው ጉዳዮች ላይ መወያየቱንና ማሻሻያ የሚያስፈልጓቸው ላይ ማስተካከያዎች እንዲካተቱ በማድረግ ረቂቅ አዋጆቹ እንዲጸድቁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲመራ ረቂቅ ደንቦቹን ደግሞ ሥራ ላይ እንዲውሉ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ