'ኑሮ ከበደኝ' ያለው ፈረንሳያዊ ወጣት እራሱን አቃጠለ

French ambulance Image copyright Getty Images

የ22 ዓመቱ ፈረንሳያዊ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እራሱን ካቃጠለ በኋላ ህይወቱ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ገብታለች።

ወጣቱ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ምክንያት ከሚማርበት ዩኒቨርሲቲ ፊትለፊት እራሱን ያቃጠለ ሲሆን ከደርጊቱ በፊት በፌስቡክ ገጹ ላይ መልዕክት አስፍሮ ነበር።

ወጣቱ በጽሑፍ 'የገደሉኝ' የአሁኑና የቀድሞ የፈርንሳይ ፕሬዝደንቶች፣ የአውሮፓ ህብረት እና ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ናቸው ሲል ተጠያቂ አድርጓቸኋል።

የሊዮን ዩኒቨርሲቲ ተማሪው በወር በ450 ዩሮ (15ሺህ ብር ገደማ) ብቻ ህይወትን መግፋት ከብዶኛል ብሏል።

እራሱን ካቃጠለ በኋላ ወደ ህክምና የተወሰደው ወጣት 90 በመቶ የሚሆነው አካሉ ከባድ ቃጠሎ አጋጥሞታል። በዚህም ህይወቱ የመትረፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል።

"አንድ ላይ በመሆን ፋሽዝምን ለመታገል ቆርጠን እንነሳ፤ ... ልዩነቶችን የሚፈጥሩ ስርዓቶችን እንታገል" ሲል ጽፏል።

"ማኽሮን [የአሁኑ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት]፣ ፍራንስዋ ኦላንድን እና ኒኮላስ ሳርኮዚን [የቀድሞ ፕሬዝደንቶች]፣ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ስለገደሉኝ ተጠያቂ የሚሆኑት እነሱ ናቸው። የወደፊት ህይወቴን አጨልመውታል" ሲል በፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።

ድርጊቱን ለመፈጸም ሰዎች የሚበዙበተን ስፍራ የመረጠውም ሆነ ብሎ መሆኑን ጠቁሟል።