በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተከሰተ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ

ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ

ትናንት ቅዳሜ ምሽት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ ሁለት ተማሪዎች መሞታቸው ተነገረ።

ያነጋገርናቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እና መምህር የብሄር መልክ በያዘው ግጭት የሁለት ተማሪዎች ህይወት ማለፉን እና በርካቶች መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል።

በዩኒቨርሲቲው መምህር የሆኑት ምንጫችን ትናንት ምሽት በተፈጠረው ግጭት ሁለት ተማሪዎች መሞታቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲው ደውለው መስማታቸውን ነግረውናል።

የሆስፒታል ምንጮች እንደጠቆሙት ደግሞ ወደ ወልዲያ ጄኔራል ሆስፒታል 14 ተማሪዎች ተጎድተው መጥተዋል።

ስማቸወን መግለጽ ያልፈለጉ የወልዲያ ጀነራል ሆስፒታል ባልደረባ ለቢቢሲ "እኔ የገባሁት ዛሬ [እሁድ] ጠዋት 2፡30 ላይ ነው። ተማሪዎቹ ጉዳት ደርሶባቸው ሲመጡ አልተመለከትኩም። ግን አሁን ከ14-15 የሚሆኑ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በሆስፒታሉ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

እኚሁ የሆስፒታል ባልደረባ በተማሪዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከቀላል እስከ ከባድ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፤ ጉዳቱ ያጋጠመው በድብደባ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጫማሪ ትናንት ምሽት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በተፈጠረባቸው የደህንነት ስጋት ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለመውጣት የሞከሩ ተማሪዎች ከግቢው እንዳይወጡ መከልከላቸውን ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ተናግረዋል።

የምስሉ መግለጫ,

ግጭቱን ተከትሎ የደህንነት ስጋት የገባቸው ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለመውጣት ሲሞክሩ መከልከላቸውን ተናግረዋል። [ፎ፡ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እሁድ ጠዋት]

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ ተማሪ ለቢቢሲ "ትናንት የተፈጸመውን አይተን እንዴት ነው ዶርም ውስጥ የምንተኛው?" ሲል ተናግሯል። ጨምሮም "ትናንት የተፈጸመው ዳግም ላለመከሰቱ ምንም ማረጋገጫ የለንም" በማለት ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ እንዳይወጡ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ጠቁሟል።

በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ዲን ፕሬዝደንት መረጃ እያጠናቀርን ነው በማለት ዝርዝር መረጃ ሊሰጡን አልቻሉም። የዩኒቨርሲቲው ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ስልክ ደግሞ ሊሠራልን አልቻለም።

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የጥበቃ እና ደህንነት ሺፍት ኃላፊ የሆኑት ሻምበል መንግሥቱ ትናንት ምሽት በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ስለተፈጸመው መረጃ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው "ምንም መረጃ የለኝም" በማለት መረጃ ከመስጠት ተቆጠበዋል።

የአማራ መገናኛ ብዙሃን በበኩሉ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንኤ መኮንን በመጥቀስ ትናንት ምሽት ተማሪዎች በጋራ እግር ኳስ በቴሌቪዝን ተመልክተው ሲመለሱ በተፈጠረ ግጭት ሁለት ተማሪዎች መገደላቸውን እና ስምንት ተማሪዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን ዘግቧል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ ተገኘተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ በተማሪዎች መካከል የተነሳውን ግጭት የብሔር ለማስመሰል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አሉ ይላሉ።

"በግጭቱ ተማሪዎች ተጎድተዋል። በአሁኑ ሰዓት ጉዳዩን አረጋግተነዋል። በዚህ ወንጀል ላይ የተሳተፉ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውለናል። አልፎም አማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ ሰላም ለማደፍረስ የሚሠሩ አካላትን ለይተን እርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀስን ነው።"

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ትናንት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተፈጸመውን ክስተት አውግዟል።

የክልሉ ምክት ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲስ ዛሬ [እሁድ] ከሰዓት በጽሁፍ በሰጡት መግለጫ፤ "እስካሁን ባለን መረጃ በሰላማዊ ተማሪዎች ላይ በተፈጸመ ድብደባ የተገሉት ተማሪዎች ቁጥር ሁለት ናቸው" ያሉ ሲሆን በበርካቶች ላይ ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱን እና በተለያዩ ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች በሁኔታው መደናገጣቸውን ጠቁመዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ፤ "አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ እና አስተሳሰቦቻቸውን በኃይል ህዝብ ላይ ለመጫን ጥረት እያደረጉ ነው" ያሉ ሲሆን፤ እንዲህ አይነት በፖለቲካ ንግድ የሰከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዘሯቸው አጀንዳዎች የኦሮሞ እና የሌሎች ብሄር ልጆች ያልተገባ መስዕዋትነት እየከፈሉባቸው ይገኛሉ" ብለዋል።

ለትናንት ምሽቱ ጥቃት ተጠያቂ ናቸው የተባሉት ለፍርድ እንዲቀርቡ ከፌደራል እና ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር አብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ፤ "ወደ ክልላችን ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተማሪዎችን ደህንነታቸወን በማስጠበቅ እንደ ልጆቻችን እንድንከባከባቸው እና የጥፋት ኃይሎች ፍላጎትን አንድናከሽፍ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ" ብለዋል።