ኢራን 53 ቢሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ማግኘቷን አሳወቀች

ኢራን 53 ቢሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ማግኘቷን አሳወቀች Image copyright Getty Images

የኢራንን የነዳጅ መጠን በሶስት እጥፍ ያሳድጋል የተባለለት 53 ቢሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ማግኘቷን ፕሬዝደንት ሃሰን ሩሃኒ አሳወቁ።

በደቡብ ምዕራቧ ኩዝስታን አውራጃ የተገኘው ድፍድ ነዳጅ 2400 ስኩዌር ኪሌሜትር የሚሸፍን ነው ብለዋል ፕሬዝደንቱ።

ኢራን ከአሜሪካ በተጣለባት ማዕቀብ ሳቢያ ነዳጅ ወደ ውጭ ልካ ለመሸጥ እየተቸገረች ትገኛለች። ማዕቀቡ የተጣለባት አምና ሲሆን አሜሪካ ከሌሎች የዓለም ኃያላን ጋር የነበራትን የኒውክሌር ስምምነት አልፈልግም ብላ ከወጣች በኋላ ነው።

«ድፍድፍ ነዳጁ 80 ሜትር ወደታች ጥልቀት ያለው ነው። የኢራን ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ብትጥሉም የሃገሪቱ ኢንጂነሮች 53 ቢሊዮን በርሜል ድፍድፍ አጊንተዋል። ይህን ለኃይት ሃውስ መናገር እፈልጋለሁ» ብለዋል ሲል የዘገበው ፋርስ የዜና ወኪል ነው።

አዲስ የተገኘው ድፍድ ነዳጅ በሃገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ የነዳጅ ክምችት ያለበት ስፍራ ይሆናል ተብሎለታል። አህቫስ የተሰኘው ስፍራ በ65 ቢሊዮን በርሜል ትልቁ ነው ይላል አሶሼትድ ፕሬስ።

Image copyright EPA

ኢራን በዓለማ ካሉ አበይት ነዳጅ አምራች ሃገራት አንዷ ናት። ከነዳጅ ሽያጭ የምታገኘው ዓመታዊ ገቢም በቢሊዮን ዶላሮች ይገመታል።

ፕሬዝደንት ሩሃኒ አሁን ላይ ሃገራቸው ያላት የድፍድፍ ነዳጅ ክምችት 150 ቢሊዮን በርሜል እንደሆነ ተናግረዋል። ይህ ደግሞ በዓለም አራተኛው ነው። ከኳታር ጋር የምታጋራው ውቅያኖስ ሥር ያለ የተፈጥሮ ጋዝ ባለቤትም ነች።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን እና ሌሎች ስድስት ሃገራት የገቡትን የኒውክሌር ስምምነት አፍርሰው ኢራን ላይ ማዕቀብ ከጣሉ በኋላ የቴህራን ምጣኔ ሃብት እያሽቆለቆለ ይገኛል።