አየር መንገዶች "ከምድራችን ይልቅ ጥቅማቸውን ያስቀድማሉ" የሚል ክስ ቀረበባቸው

British Airways

በብሪቲሽ አየር መንደገድ ውስጥ የሚሰራ አንድ የዘርፉ ባለሙያ እንዳጋለጠው፤ በአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሆነ ተብሎ አውሮፕላኖች ብዙ ነዳጀ ጭነው እንዲጓዙ ይደረጋል።

ይህም አውሮፕላኑ በሚይዘው ክብደት ልክ ብዙ ነዳጅ ተቃጥሎ አየር እንዲበከል እየተደረገ ነው ተብሏል።

አየር መንገዶች አውሮፕላኖቻቸው ከመነሻቸው ብዙ ነዳጅ ጭነው የሚነሱት በመዳረሻ አየር መንገዶች ለነዳጅ የሚጠየቁትን ብዙ የነዳጅ ገንዘብ ለማስቀረት ነው።

ብሪቲሽ አየር መንገድ "ለደህንነት እና ከዋጋ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች" ተጨማሪ ነዳጅ ይዞ መብረር የተለመደ ነው ብሏል።

ቢቢሲ ፓኖራማ የተሰኘው የቢቢሲ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ባለፈው ዓመት የብሪቲሽ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ተጨማሪ ነዳጅ ይዘው በመብረራቸው ተጨማሪ 18ሺህ ቶን ካርበን ዳይኦክሳይድ አመንጭተዋል ሲል መዘገቡ ይታወሳል።

አንድ ጥናት እንዳረጋገጠው ደግሞ አውሮፓ ውስጥ ከሚደረጉ ከአምስት በረራዎች ቢያንስ በአንዱ አውሮፕላኑ ተጨማሪ ነዳጅ ይዞ ወደ መዳረሻው ይበራል።

ተቺዎች እንደሚሉት ይህ ተግባር አየር መንገዶች የአየር ብክለትን ለመቀነስ እንሰራለን የሚሉትን ቃል ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው።

ከተቺዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት ጆህን ሳኡቨን አየር መንገዶች "ከምድራችን ይልቅ ጥቅማቸወን ያስቀድማሉ" ለምንለው ይህ ትክክለኛ ማሳያ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።