ጋምቢያ ከሮሂንጋ ሙስሊሞች ጋር በተያያዘ ሚያንማርን ልትከስ ነው

የጋምቢያ ዋና አቃቤ ሕግ እና ጠበቃ የሆኑት አቡባካር ታምባዶ ምያንማር የሮሂንጃ ሙስሊም ዜጎቿ ላይ የምትፈፅመውን ግፍ ታቁም ይላሉ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የጋምቢያ ዋና አቃቤ ሕግ እና ጠበቃ የሆኑት አቡባካር ታምባዶ ምያንማር የሮሂንጃ ሙስሊም ዜጎቿ ላይ የምትፈፅመውን ግፍ ታቁም ይላሉ

ትንሿ ምዕራብ አፍሪቃዊት አገር ጋምቢያ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት በማቅናት ሚያንማርን ከሳለች።

ወደ ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የተላከው ክስ የሚያንማር መንግሥት የሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሟል ሲል ይነበባል።

ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ዘገባ የሚያንማር ወታደራዊ መኮንኖች በሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ በፈፀሙት ወንጀል ፍርድ አደባባይ ሊቆሙ ይገባል ማለቱ ይታወሳል።

የሚያንማር መንግሥት 'ወታደሮቼ ምን በወጣቸው እንዲህ ዓይነት ወንጀል የሚፈፅሙት' ሲል ዘገባውን ማጣጣሉ አይዘነጋም።

በግሪጎሪ አቆጣጠር 2017 ላይ የሚያንማር መንግሥት የሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ በወሰደው እርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸው ሲያልፍ 700 ሺህ ገደማ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገር ባንግላዴሽ ተሰደዋል።

የተባባሩት መንግሥታት የቀጠረው አንድ እውነታ አጣሪ ቡድን የሚያንማር መንግሥት ወታደሮች የሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ ያልተገባ እርምጃ ወስደዋል ሲል ይፋ አድርጎ ነበር። እየለዩ መግደል፣ በጅምላ አስገድዶ መድፈር፣ ሕፃናትን መበዝበዝ እና መንደር ማቃጠል ወታደሮቹ የተከሰሱባቸው ወንጀሎች ናቸው።

ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት [አይሲሲ] ሚያንማር ላይ ይፋ ምርመራ ይደረግ ዘንድ ቢያዝም አገሪቱ የአይሲሲ አባል አለመሆኗ ነገሮችን አክብዷል።

አብዛኛው ዜጋዋ ሙስሊም የሆነው ጋምቢያ ጉዳዩን ወደ ሄግ የወሰደችው ሰኞ ዕለት ነው። ጋምቢያ 57 አባላት ካሉት የእስላማዊ አገራት ትብብር እና ከዓለም አቀፍ ጠበቃዎች ድጋፍ ማግኘቷ ተነግሯል።

የጋምቢያ ዋና አቃቤ ሕግ እና ጠበቃ የሆኑት አቡባካር ታምባዶ ምያንማር የሮሂንጃ ሙስሊም ዜጎቿ ላይ የምትፈፅመውን ግፍ እንድታቆም ጠይቀው ክሱን እንደሚገፉበት አስታውቀዋል።

ከባንግላዴሽ ጋር በምትዋሰነው የራካይን ግዛት የሚኖሩት የሮሂንጃ ሙስሊሞች ከአብዛኛው የቡድሃ እምነት ተከታይ የሚያንማር ዜጋ ለየት ያለ ቋንቋ እና ባሕል አላቸው።

ሚያንማር ውስጥ ይኑሩ እንጂ በሚያንማር ባለሥልጣናት እንደዜጋ ተቆጥረው አይታወቁም፤ የሕዝብ ቆጠራ እንኳ የመሳተፍ የዜግነት መብት የላቸውም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ