የሌሶቶ መንግሥት ኢቦላን አስመልክቶ ያሠራጨው ሃሰተኛ ዜና ሃገሩን አሸበረ

የሌሴቶ መንግሥት ኢቦላን አስመልክቶ ያሠራጨው ሃሰተኛ ዜና ሃገሩን አሸበረ Image copyright Getty Images

ከደቡብ አፍሪቃ ጋር የምትዋሰነው ሌሶቶ በተሠራጨ ሃሰተኛ ዜና ነዋሪዎች ተሸብረው ውለዋል።

የሌሶቶ መንግሥት ያሠራጨው ሃሰተኛ ዜና አንዲት በኢቦላ ቫይረስ የተያዘች ሴት ሃገራችን ገብታለች ተጠንቀቁ ይላል።

የደቡብ አፍሪቃዊቷ ሃገር መንግሥት ይህን ዜና ያሠራጨው ዜጎች ኢቦላ ቢከሰት ምን ያህል ዝግጁ ሆነው ይጠብቃሉ የሚለውን ለማየት ነው ተብሏል።

ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አንዲት ደቡብ አፍሪቃዊት ሴት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ሰው ጋር ተነካክታ የኢቦላ ቫይረስ ተጠቂ ሆናለች፤ ወደ ሃገራችንም ገብታለች ሲሉ ተናገሩ።

ይህን የሰሙ ጋዜጦች በፊት ገፃቸው ዜናውን ይዘው ወጡ። ቴሌቪዥኖችም አስተጋቡ። ራድዮኖችም ሃገር ተጠንቀቅ ሲሉ ዘገቡ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ደቡብ አፍሪቃዊቷ ሴት ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተደረገላት መሆኑን አሳውቀው ነበር።

ትንሽ ቆይቶ ግን የሃገሪቱ ተላላፊ በሽታዎች መከላከል መሥሪያ ቤት የተሠራጨው ዜና ሃሰት ነው ማንም የኢቦላ ተጠቂ የሆነ ሰው ሌሶቶ አልገባም ሲል አሳወቀ።

መሥሪያ ቤቱ መንግሥት ሃሰተኛውን ዜና ያሠራጨው ዜጎች ወደ ሆስፒታል ሄደው ለመመርመር ምን ያህል ዝግጁ ናቸው የሚለውን ለማዬት ነው ብሏል።

ብዙዎችን ያስደነቀው የጤና ሚኒስትሩ ኢቦላ ሌሶቶ ገባ የሚባለው እውነት ነው ወይ የሚለውን ለማጣራት መገናኛ ብዙሃን ሲደውሉላቸው 'በትክክል' እያሉ መመለሳቸው ነው።

ጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ከሰዓታት በኋላ ሌላ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ