“ከብሔርም ከሐይማኖትም በላይ ሰውነት ከሰሃራ በረሃ ስቃይ አውጥቶኛል"

ሃሩን አሕመድ Image copyright Harun Ahimad
አጭር የምስል መግለጫ "በብሔርና በሃይማኖት ያቻቻለን የሰሃራ በረሃ ስቃይ" ሃሩን አሕመድ

ከሰሃራ በረሃ ሃሩር፣ ከደላሎች ዱላና እንግልት ተርፎ ጀርመን የሚኖረው ሃሩን አሕመድ፣ በበረሃው ውስጥ አቅም አጥቶ ሲወድቅ የደገፉትን፣ ሲታረዝ ያለበሱትን፣ በውሃ ጥም የከሰለ ከንፈሩን ያረሰረሱለትን ሲያስታውስ "የሰው ልጅ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ተቻችሎ መኖር እንዳለበት ብዙ ተምሬያለሁ" ይላል።

በባሌ ዞን አጋርፋ የተወለደው ሃሩን፣ እንደማንኛውም ወጣት በፖለቲካ ምክንያት ችግር ቢደርስበትም እርሱ ግን "ከሀገር የወጣሁት በግል ምክንያት ነው" ይላል።

እኤአ በ2013 ከሻሸመኔ ተነስቶ ወደ ሱዳን አመራ። ከአንድ ዓመት የሱዳን ኑሮ በኋላ እዚያ ከሚገኙ ከአራት ጓደኞቹና ከሌሎች ስደተኞች ጋር በ2014 መጀመሪያ ወደ ሊቢያ ጉዞ ጀመሩ።

ህወሓት፡ ሃገራዊ ምርጫ የሚራዘም ከሆነ ትግራይ የራሷን ምርጫ ታካሂዳለች

"ከካርቱም ትንሽ ወጣ ያለ ቦታ ላይ ከኤርትራዊያን፣ ሶማሊያዊያንና ሱዳናዊያንና ከኢትዮጵያ ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ ስደተኞች ጋር ሰበሰቡን" ሲል በወቅቱ የነበረውን ያስታውሳል።

ስቃያችን የጀመረው ገና ከካርቱም ስንነሳ ነው የሚለው ሃሩን፤ ሁሉንም በጋራ የሰበሰቡበት ስፍራ ከመድረሳቸው በፊት የያዙትን አራግፈው እንደወሰዱባቸው ሲናገር "ሴቶችን ልብስ አስወልቀው ጭምር ነበር የፈተሿቸው" በማለት ወርቅና ገንዘባቸውን እንደወሰዱባቸው ይገልጻል።

ሁለት ቀን እዚያ በረሃ ውስጥ ካሳደሯቸው በኋላ ወደ ሰሃራ የሚወስደዳቸው ግለሰብ መጥቶ መንገድ ጀመሩ።

በአንድ መኪና ላይ ከ90 በላይ ሰዎች ሲጫኑ ሁሉም እንደትውውቃቸው፣ እንደመጡበት ሀገርና አካባቢ ብሔራቸውን ጭምር መሰረት አድርገው መቧደናቸውን ያስታውሳል።

እሷ ማናት፡ ዘቢብ ካቩማ "ለዩኤን እሠራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም"

አራት ቀንና ሌሊት ከተጓዙ በኋላ መኪናዋ ላይ የተሳፈሩ ስደተኞች ጥል እየተካረረ መጣ።

ሰዎች ከፍርሃትና ከተስፋ መቁረጥ የተነሳ የራሳቸውን ምግብና ውሃ እየደበቁ የሌላ ግለሰብ ስንቅ መስረቅ በመጀመራቸው አለመግባባቱ ወደ ድብድብ አደገ።

መጎሻሸሙ፣ ቡጢውና ጉልበት መፈታተሹ እርስ በእርስ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰሃራ ይዟቸው እየሄደ ከነበረው ግለሰብ ጋርም ሆነ።

ጉዞ በጀመሩ በሰባተኛው ቀን ሱዳን፣ ግብጽንና ሊቢያን የሚያዋስነው ድንበር ላይ ስደተኞችን የሚለዋወጡበት ስፍራ ደረሱ።

ስፍራው ላይ ሲደርሱ ግን እድል ከእነርሱ ጋር አልነበረችም።

ከሊቢያ ሊቀበላቸው የመጣው ግለሰብ በታጣቂዎች ተይዞ ጠበቃቸው።

ቀደም ብሎ እኔ ስለተያዝኩ አታምጣቸው ብሎ ይዞን እየሄደ ለነበረው ሰው መልዕክት ልኮለት ነበር የሚለው ሃሩን "እርሱ ግን ከእኛ ጋር ተጣልቶ ስለነበር የራሳቸው ጉዳይ በሚል ስሜት ነበር ይዞን ሄደ" ይላል።

በሦስቱ ሃገራት ድንበር ላይ ሲደርሱ ወደ ስምንት የሚሆኑ መኪኖች ከብበዋቸው፣ መሳሪያ ከደቀኑባቸው በኋላ እነ ሃሩንንም ሆነ ከሱዳን ይዟቸው የሄደውንና ከሊቢያ ሊወስዳቸው የመጣውንም አንድ ላይ ወሰዷቸው።

መሳሪያ መታጠቃቸውን እንጂ ምን እንደሆኑና ማን እንደሆኑ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ የሚገልፀው ሃሩን ከበርሃ ወጥተው እንደከበቧቸው ያስታውሳል።

"እነዚህ ታጣቂዎች ያለምንም ምግብና ውሃ ሁለት ቀንና ሌሊት ይዘውን ከሄዱ በኋላ የማይታወቅ በረሃ ውስጥ አወረዱን። ለአንድ ሰው 5ሺህ ዶላር ካልከፈልን ከዚያ መንቀሳቀስ እንደማንችል ነገሩን። እኛ ብቻ ሳንሆን ከሊቢያ ሊወስደን የመጣው ሰውዬም ያለንበትን ስፍራ አያውቀውም ነበር።"

ኢትዮጵያ ወይስ ናይጄሪያ? የትዊተር አለቃ የፈጠረው ክርክር

ከዚህ በኋላ 5ሺህ ዶላሩን መክፈል የምትችሉ መኪና ላይ እንዲወጡ የማይችሉ ግን እዚያው እንዲቆዩ ተነገራቸው።

ኤርትራዊያንና ሱዳኖች እንከፍላለን ብለው መኪና ላይ መውጣታቸውን የሚናገረው ሃሩን፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊያኖች ግን ገንዘብ ለመክፈል እንደማይችሉ ተናግረው እዚያወቅ ለመቆየት መወሰናቸውን ያስታውሳል።

በኋላም ኤርትራዊያኑንና ሱዳናዊያኑን ይዞ የሄደው መኪና መንገድ ከጀመረ በኋላ ተመልሶ በመምጣት በመሳሪያና በዱላ እያስፈራሩ መኪናው ላይ እንዳሳፈሯቸውና እንደወሰዷቸው ይናገራል።

አጭር የምስል መግለጫ ሃሩን አህመድ የተጓዘበት መስመር

ጉዞ ወደ ሊቢያ

ሦስት ቀን ያለማቋረጥ ከተጓዙ በኋላ አንድ ቦታ መድረሳቸውንወ የሚናገረው ሃሩን፤ ስፍራው ሰዎች እንደ ባሪያ የሚሸጡበት መሆኑን ያስታውሳል።

ስፍራው ላይ ከደረሱ አራት ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸው፣ ልብሳቸው ላያቸው ላይ የነተበ፣ ሰው የማይመስሉ ከ200 በላይ ስደተኞች፣ አብዛኛዎቹ ሶማሊያዊያን መሆናቸው ማግኘታቸውን ያስታውሳል።

"እዚያ እንቆያለን ብለን ስላላሰብን የቀረችንን ስንቅም ውሃም ሰጠናቸው።"

እነሃሩን እንዳሰቡት ሳይሆን የስደተኛ አቀባባዮቹ እንደፈቀዱት ሆነ።

"ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበት ዋጋ ያላገኘሁበት ቢኖር ትምህርት ነው"

ይዘዋቸው የመጡ ታጣቂዎች አራት አራት ሺህ ዶላር ካልከፈሉ በስፍራው እንዳቆይዋቸው እና ከሰውነት ጎዳና የወጡ ስደተኞች እንደሚሆኑ በመንገር አስፈራሯቸው።

ማስፈራራቱ ከስፍራው ባለመንቀሳቀስ ጸና። ቀና ቢሉ ጠራራ ጸሀይ፣ ዞር ቢሉ ጎስቋላ ስደተኛ፣ ድካም ያዛለው፣ ውሃ ጥም ያቃጠለው የሀገር ልጅ በሚያዩበት ምድረ በዳ መጋዘን ተገኝቶ እዚያ ውስጥ ታሰሩ።

አሳሪዎቻቸው እጃቸው የተፈታ ቀን፣ በቀን አንዴ ሆዳቸው የጨከነ እለት ደግሞ፣ በሁለት ቀን አንዴ ምግብ ይሰጧቸዋል።

"ሌሊት ሌሊት ደግሞ ይደበድቡናል" የሚለው ሃሩን በአጠቃላይ ለአራት ወራት በዚያ ስፍራ መታሰራቸውን ይናገራል።

አራት ወር ሲሞላቸው ልብሳቸው አልቆ፣ አብረዋቸው ከተሰደዱት ጋር ተረሳስተው፣ የት ለመሄድ እንደሚፈልጉ ዘንግተው እስትንፋሳቸውን ማቆየት ብቻ የህይወት ግባቸው ሆኖ እንደነበር ይናገራል።

"በዚህ ስፍራ በረሃውንና የደረሰባቸውን ድብደባና ስቃይ መቋቋም ያቃታቸው አንድ ኢትዮጵያዊ ጓደኛችንን ጨምሮ አስራ ሁለት ሶማሌያዊያንን ቀብረናል።"

በዚህ ሁሉ ስቃይ ውስጥ ይላል ሃሩን የመጡበት ሃገርን፣ ብሔራቸውንና ዘራቸውን ዘንግተው ሰው መሆናቸውን ብቻ ያስታውሱ እንደነበር የሚናገረው ሃሩን በመካከላቸው መደጋገፉና መረዳዳቱ ጠንካራ እንደነበር ይናገራል።

የመረዳዳታቸውን ጣሪያ ሲያስታውስ ከመካከላቸው አንድ ሰው በውሃ ጥም ሞቶ ለሌሎች ከንፈራቸውን የሚያረጥቡበት ውሃ እንዲያገኙ ለማድረግ እስከመፍቀድ እንደነበር ይገልጻል።

Image copyright AFP

የኩላሊት ገበያ

"አንድ ቀን..." ይላል ሃሩን "ኩላሊት የሚገዙ ሰዎች ወደ ታሰርንበት መጋዘን መጡ" የሚገዛው ግለሰብ ግን የበረሃው ሃሩርና ውሃ ጥም ያከሰላቸውን ስደተኞች ተመልክቶ፣ እነዚህማ ለራሳቸውም ደክመዋል ምንስ ኩላሊት አላቸው በማለት ትቷቸው መሄዱን ይጠቅሳል።

ስደተኞቹ ኩላሊታቸው ተሸጦ ዋጋ እንደማያወጡ፣ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ልከውም እንደማይከፈላቸው የተረዱት ደላሎች ለሌላ ነጋዴ አሳልፈው ሸጧቸው።

የገዛቸው ሰው ለእያንዳንዳቸው ሦስት ሺህ ዶላር እንዳወጣና ገንዘቡን እንዲከፈለው እንደሚፈልግ ቀጭን ማሳሰቢያ አዘል ማስፈራሪያ ተናገረ።

በበረሃው የተዳከሙ፣ በተስፋ መቁረጥ የሚዋልሉ ስደተኞች 'ከዚህ ብቻ አውጣን እንጂ እንከፍልሃለን' በሚል ተስማምተው አብረውት ሄዱ።

ከዚህ ሰውዬ ጋር ቀንና ሌሊት ለአራት ቀን ከተጓዙ በኋላ ሳባ የምትባል የሊቢያ ከተማ ላይ ደረሱ።

የሴቶች ዘብ የነበሩት ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ

ይዘዋቸው የሚሄዱት ሰዎች የደረሱበትን የሚያውቁት ካርታ ዘርግተው፣ የፀሐይን አቅጣጫ አይተው ወይንም ነዋሪውን ጠይቀው አይደለም። አሸዋውን ዘገን አድርገው ብቻ የት ሃገር እንደደረሱ ይናገራሉ።

ዓይን ማየት የቻለበት ርቀት ሁሉ አሸዋ ለሆነበት ስደተኛ፣ የአንዱ ሀገር አሸዋ ከሌላኛው ሀገር የሚለይበት መልክ አይገለጥለትም። ለሀገሬው ግን አቅጣጫ ጠቋሚ፣ ሀገር አመላካች ነው።

እነ ሃሩንን ሳባ የወሰዳቸው ግለሰብ በከተማዋ እንደ ሃገረ ገዢ እንደሚታይ ግን ማወቅ ችለዋል። የተጠየቀውን ገንዘብ የከፈለ ስደተኛ በሳባ ውስጥ እንዳሻው የመውጣት የመግባት ነጻነትን ይጎናጸፋል።

"እኛ ግን ገንዘብ ስላልነበረን" ይላል ሃሩን "ትልቅ መጋዘን ውስጥ አስገባን።"

ገንዘብ የሌላቸውና መጋዘን ውስጥ የታጎሩት እነሃሩን የተፈጠሩበትን ቀን እስኪረግሙ ድረስ ድብደባ ይደርስባቸው ጀመር።

"ወገባችንን በብረት፣ እጆቻችንን ወደኋላ አስረው እየደበደቡ ውሃ የተሞላ በርሜል ውስጥ በጭንቅላታችን ዘቅዝቀው ይከቱንና ከዚያ አውጥተው ቤተሰቦቻችን ጋር ደውለን ገንዘብ እንድናስልክ ስልክ ይሰጡናል" ሲል ያስታውሰዋል።

በዚህ ሁኔታ ቤተሰቦቻችን ጋር ደውለን ያላቸውንም ሸጠው ተበድረውም ሆነ ተለቅተው ገንዘብ ይልኩልን ነበር።

ቀድሞ ገንዘብ ከቤተሰቡ የሚላክለት ሰው ቀደሞ ከዚያ አሰቃቂ እስር ቤት የሚወጣ ሲሆን ቀሪው ግን እስኪላክለት ድረስ እዚያው ይቆያል።

ሃሩን በዚህ ስፍራ አንድ ወር ቆየ።

ከእርሱ ቀድመው የወጡ የበረሃ ጓደኞቹ፣ እንዲሁም ቤተሰቡ ያላቸውን ሳንቲም በማዋጣት ሦስት ሺህ ዶላር መክፈሉን ይናገራል።

እዚህም በገንዘብም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ሲተጋገዙ፣ ብቸኛው ግምት ውስጥ የሚያስገቡት አብረው የሚያሳልፉትን የሰቆቃ ጊዜያት፣ ሰው መሆናቸውን እንጂ መነሻቸው ላይ የነበረው የአንድ አገር ልጅነት እንዳልነበር ይናገራል።

ኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃን የተመለከተ አዋጅን ልታጸድቅ ነው

"መጀመሪያ ላይ በቋንቋ በብሔር በሃይማኖትና በዘር ስንጣላ የነበርን ሰዎች ከዚያ ሁሉ ስቃይ ሁሉ በኋላ የቀረልን ሰው መሆናችን ብቻ ነበር።"

ሰው መሆን ከሁሉ ነገር በፊት የሚቀድም መሆኑ የገባኝ ያኔ ነበር በማለትም ከእስር ቤቱ ቀድመው የወጡ እንዴት እንደረዷቸው ያስረዳል።

ሳባ ከነበረው እስር ቤት ቀድማቸው የወጣች ጽጌ የምትባል ኤርትራዊት ለቤተሰቦቻቸው በመደወል ገንዘብ እንዲላክላቸውና የጎደላቸውን ከሌሎች በማሟላት እንዲወጡ እንዳገዘቻቸው ይመሰክራል።

በዚህ መደጋገፍና መረዳዳት መካከል አዲስ አሸናፊ ከምትባል ልጅ ጋር ፍቅር ጀመረ።

እርሱ የእስልምና ዕምነት ተከታይ ሲሆን እርሷ ደግሞ ክርስትያን ነበረች። ነገር ግን እዚያ በነበረው እንግልትና ስቃይ ሁለቱ ወጣቶች በፍቅር ተጋመዱ።

"እስር ቤት ውስጥ በጭካኔና በኃይል የሚደበደቡት ወንዶች ስለነበሩ ለእርሷ የተላከላትን ገንዘብ ለእኔ ከፍላ እኔ እንድወጣ አደረገች" በማለት የሁለቱ የፍቅር ታሪክ በራሱ በተቃርኖ ውስጥ ሲጋጩ ለሚኖሩ ሌሎች ትምህርት እንደሚሆን ያነሳል።

ትሪፖሊ

ሃሮን ፍቅረኛውና ቤተሰቦቹ በማዋጣት በከፈሉት ገንዘብ ሳባ ከሚገኘው እስር ቤት ከወጣ በኋላ ወደ ትሪፖሊ ጎዞ ጀመረ።

ነገር ግን በክፉ አጋጣሚ ትሪፖሊ ከመድረሱ በፊት በሌሎች ሰዎች እጅ ወድቆ እስር ቤት ተወረወረ።

እነዚህ አሳሪዎቹ በቀን አንዴ ደረቅ ዳቦ እየሰጧቸው፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ ገንዘብ አምጡ እያሉ እደበድቧቸው እንደነበር ይናገራል።

ፍቅረኛውን አዲስን ጨምሮ ሌሎች ከሱዳን አብረው የተነሱና ሳባ አብረው ታስረው የነበሩ ስደተኞችም በሂደት ተቀላቀሏቸው። ከ18 ቀናት እስር በኋላ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተረዳድተው ስድስት ስድስት መቶ ዶላር በመክፈል ተለቀቁ።

ከዚህ በመቀጠል ያመሩት በቀጥታ ትሪፖሊ ክሪሚያ የምትባል ስደተኞች በብዛት የሚያርፉባት መንደር ነበር።

"ሶስት ጊዜ ለተለያዩ ነጋዴዎች ተሽጫለሁ"

ክሪሚያ ወደ አውሮፓ በባህር ለማቋረጥ ወረፋ የሚጠብቁና ከባህር ላይ ተይዘው የተመለሱ ስደተኞች በብዛት ያሉባት መንደር ናት።

ሃሩንና አዲስ ያገኙትን እየሰሩ ለእለት ጉርስ ለነገ ደግሞ ስንቅ እያኖሩ ከሌሎች መንገድ ላይ ከተዋወቋቸው ሰዎች ጋር ቤት ተከራይተው ለሰባት ወራት በክሪሚያ ኖሩ።

በሰባት ወር ቆይታቸው በመንደሯ በየዕለቱ የሚሰማው ወሬ የባህር ተሻጋሪ ስደተኞች ሞት አልያም በሰላም ወደ አውሮፓ መሻገር ነበር።

ይህንን በየማለዳው የሚሰሙት ሃሩንና አዲስ በየሃይማኖታቸው በሰላም የሜዴትራኒያንን ባህር ተሻግረው የሚያልሙት አውሮፓ እንዲደርሱ ይጸልዩ ነበር።

"በወቅቱ..." ይላል ሃሩን "አንዳችን የሌላኛችንን ሃይማኖት ለማስቀየር ወይም እንደ ክፍተት በመቁጠር ተነጋግረን አናውቅም።"

ክሪሚያ የከተመ ስደተኛ ሰርቶ ያገኘውን አጠራቅሞ፣ ቤተሰብ የላከለትን ቋጥሮ ሲሞላለት፣ በጀልባ ተሳፍሮ ወደ አውሮፓ ጉዞ ይጀምራል።

ያንን ሁሉ በረሃ አቋርጠው፣ ስቃይና እንግልቱን ችለው ክሪሚያ የደረሱ መጥፎ ዕጣ ከገጠማቸው ሜዴትራኒያን ባህር ውስጥ ሰጥመው ይሞታሉ።

ሃሮንም በዚህ ሁኔታ ብዙ ሰው ነው ያለቀው በማለት "ባህር ውስጥ ሰጥመው የሞቱ በርካታ ጓደኞቻችን አሉ" ይላል።

መጀመሪያ በባህር ወደ ጣሊያን ከዚያም ወደ ጀርመን ያቀናውና አሁን እዚያ የሚኖረው ሃሩን፤ በሃይማኖት በብሔር ወገን ለይቶ መጠላላትና መጋደል አስፈላጊ እንዳልሆነ በመግለጽ የእርሱ የስደትና የመከራ ሕይወት ይህንን እንዳስተማረው ይገልጻል።

ሃሩንና አዲስ በስደት እያሉ አንድ ልጅ የወለዱ ሲሆን ጀርመን ከገቡ በኋላ ሁለቱም በየሃይማኖታቸው ለመቆየት በመወሰናቸው፣ ልጃቸውን በጋራ ለማሳደግ ተስማምተው ለየብቻቸው እየኖሩ ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ