ኢራን የነዳጅ ዋጋ መናርን ተቃውመው አደባባይ የወጡ ዜጎቿን አስጠነቀቀች

Iranian protesters block a road during a demonstration against an increase in gasoline prices in the central city of Shiraz on Image copyright AFP

የኢራን አገር ውስጥ ሚኒስቴር የነዳጅ ዋጋ መናርን ተቃውመው አደባባይ የወጡ ዜጎች ላይ ወታደራዊ ኃይል ሊዘምት ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።

የኢራን መንግሥት የነዳጅ ዋጋን ድንገት በመጨመሩ ምክንያት ነው በሃገሪቱ ተቃውሞ የበረታው።

እስካሁን በነበረው ተቃውሞ ቢያንስ አንድ ሰው ሞቷል፤ በርካቶችም በፖሊስ ዱላ መቁሰላቸው ተዘግቧል።

ባለሥልጣናት የነዳጅ ዋጋን ቢያንስ በ50 በመቶ መጨመሩ ያስፈለገው በሚገኘው ገንዘብ ድሆችን ለመርዳት ነው ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የማዕቀብ ዱላ ያረፈባት ኢራን ምጣኔ ሃብት ከማዕቀቡ በኋላ እየተጎዳ እንደመጣ ይነገራል። አሜሪካ ኢራን ላይ ማዕቀብ የጣለችው ባለፈው ዓመት፤ ኢራንን ጨምሮ ሌሎች ኃያላን አገራት ከፈረሙት የኒውክሌር ስምምነቱ ከወጣች በኋላ እንደነበር አይዘነጋም።

አርብ ዕለት መንግሥት የነዳጅ ዋጋ መናሩን ካወጀ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው የተቃውሞ ድምፅ አደባባይ ላይ ይሰማ የጀመረው። ተቃውሞው ቅዳሜም ቀጥሎ በርካታ የአገሪቱ ክፍሎችን ማዳረስ ይዟል።

የኢራን መንግሥት የበይነ-መረብ አገልግሎት ሳያቋርጥ አልቀረም የሚል ዘገባ ሮይተርስ የተሰኘው ዜና ወኪል አስነብቧል።

ሚኒስትር አብዶልሬዛ ራሃማኒ-ፋዚል ከሃገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው ተቃውሞው የሚቀጥል ከሆነ የፀጥታ ኃይሎች ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ከማስቆም ውጭ አማራጭ አይኖራቸውም ሲሉ የተደመጡት።

ሚኒስትሩ 'የተወሰኑ ሰዎች' አጋጣሚውን ተጠቅመው ሽብር እና ማስፈራራት እየፈጠሩ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

በተቃውሞው ምክንያት አንድ ሰው መሞቱ ይነገር እንጂ ሌሎችም ሕይወታቸው ሳይልፍ እንዳልቀረ ተሰግቷል። ማሕበራዊ ድር-አምባዎች ላይ የሚውጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም በርካታ የሃሪቱ ክፍሎች ሰላም እንደራቃቸው ያሳያሉ።

በጭማሪው መሠረት በ10 ሺህ የኢራን ሪያል ይገዛ የነበረው አንድ ሊትር ነዳጅ 30 ሺህ ገብቷል። አልፎም ነዳጅ ፈላጊዎች በወር ከ60 ሊትር በላይ ነዳጅ መሸመት አይችሉም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ