ንጉሡን ወቅሶ ዘፈን የለቀቀው ሞርኳዊ 'ራፐር' የሁለት ዓመት እስር ይጠብቀዋል

ንጉሱን ወቅሶ የዘፈነው 'ራፐር' የሁለት ዓመት እሥር ይጠብቀዋል Image copyright FACEBOOK/GNAWI

የሞሮኮ ንጉሥን ወቅሶ የራፕ ሙዚቃ የለቀቀው ዘፋኝ ተከሷል።

የዛፋኙ እሥራት በሞሮኳዊያን ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል፤ ምንም እንኳ ፖሊስ የታሠረው ከሙዚቃው ጋር በተያያዘ አይደለም ቢልም።

ግዋኒ በተሰኘ ቅጽል ስሙ ይታወቃል፤ ሞሐመድ ሙኒር የተባለው 'ራፐር'። በያዝነው ወር መባቻ አካባቢ ነበር በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው። የዛሬ ሳምንት ፍርድ ቤት የሚቀርበው ግዋኒ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የሁለት ዓመት እሥር ሊጠብቀው ይችላል።

ራፐር ግዋኒ የሞሮኮ ንጉሥን እየወቀሰ ዘፈን በለቀቀ ሁለተኛ ቀን ነበር የፖሊስ ካቴና ሲሳይ የሆነው። ፖሊስ ዘፋኙ ለእሥር የተዳረገው ንጉሡን በመውቀሱ ሳይሆን ፖሊስ በመሳደቡ ነው ይላል።

የግዋኒን እሥር ተከትሎ የተቃውሞ ድምፆች መሰማት ጀምረዋል። አምነስቲ የተሰኘው የመብት ተቆርቋሪ ቡድን የዘፋኙን እሥር የንግግር ነፃነት ላይ የተቃጣ አደጋ ሲል ገልፆታል።

ሞሮኳዊያን 'ሎንግ ሊቭ ዘ ፒፕል' [በግርድፍ ትርጉሙ 'ሕዝብ ለዘላለም ይኑር'] የተሰኘው የራፕ ሙዚቃ 'ንጉሡ ለዘላለም ይኑሩ' የሚለውን የሚፃረር በመሆኑ ነው ግዋኒ ለእሥር የተዳረገው ሲሉ ያምናሉ።

13 ሚሊዮን የዩቲዩብ ተመልካች ያገኘው ሙዚቃ ሞሮኮ ውስጥ ተንስቶ ስለነበረው ሕዝባዊ አመፅ እና ስለአረብ ስፕሪንግ ያነሳል። አልፎም በፖለቲካ ምክንያት ዘብጥያ ስለወረዱ ሞሮኳዊያን ያወሳል።

ሞሮኮ ውስጥ 'ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ' አባባል ብቻ አይደለም። ንጉሡን መውቀስ በሕግ ያስቀጣል አሊያም ያስገላምጣል። ሞሮኮ ንጉሡን መውቀስ እንደ ነውር የሚቆጠርባት ሃገር ናት።

ተያያዥ ርዕሶች