ታይሮን ሚንግስ፡ ከመጠጥ ቀጅነት ወደ እንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን

Tyrone Mings on leaving non-league to join Ipswich Town.

መጠጥ ቀጅነት፤ ቤት አሻሻጭ፤ እንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን።

ከ10 ዓመት በፊት ሳውዝሃምፕተኖች ቀጫጫ ነው በማለት ያሰናበቱት ወጣት ዛሬ [እሁድ ኅዳር 7] ደግሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ወክሎ ይጫወታል፤ ታይሮን ሚንግስ።

ታድያ በእነዚህ 10 ዓመታት ብዙ አሳልፏል። ለጠጪዎች መጠጥ ቀድቷል። የ100 ፓውንድ መኪናውን እያሽከረከረ ሰዎች ከባንክ የቤት መሥሪያ ብድር እንዲወስዱ አስማምቷል።

ኢፕስዊች ታውን ለተሰኘው ክለብ መጫወት ፈልጎ ሳይታመም አሞኞል ብሎ ከሥራ ቀርቷል በሚል ቅጣት ድርሶበታል። ከአየርላንድ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ጋር ቡጢ ቀረሽ ቁርሾ ነበረው።

ጉዞ ወደ ኮሶቮ

ሚንግስ አሁን ለሚጫወትበት አስቶን ቪላ የፈረመው በውሰት ከመጣበት ቦርንመዝ ነው። የ26 ዓመቱ ተከላካይ ዘንድሮ የተቀላቀለው ፕሪሚዬር ሊግ ብዙ የከበደው አይመስልም።

195 ሴንቲሜትር የሚረዝመው ተከላካዩ ሚንግስ በፕሪሚዬር ሊግ ብዙ ኳሶችን ከግብ ክልሉ በማራቅ [ክሊራንስ] ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የአካዳሚ ጓደኛው አሌክስ ኦክስሌድ-ቻምበርሌይን ነገሮች ተመቻችተውለት ታላላቅ ክለቦችን እየቀያየረ አሁን ሊቨርፑል ሲደርስ ሚንግስ ግን ብዙ ክለቦች አንፈልግህም እያሉ አባረውታል።

ብሪስቶል ሮቨርስ አታዋጣንም ብለው ያባረሩት ሚንግስ ወደ ተማረበት ት/ቤት ተመልሶ መጫወት ጀመረ። በወቅቱ አንድ ባር ውስጥ መጠጥ ቀጅ ነበር። ቀን ቀን ደግሞ ለባንክ ቤት በኮሚሽን ተቀጥሮ የቤት ኪራይ ብድር ያስማማ ነበር። ታድያ በዚህ ጊዜ ያልተለየችው በደጉ ዘመን የሸመታት የ100 ፓውንድ [በአሁኑ ገበያ 3,700 ብር ገደማ] መኪናው ነች።

ከዚያ ኢፕስዊች ታውን ለሙከራ ጊዜ ብሎ ወሰደው። ነገር ግን የወቅቱ የቡድኑ አሠልጣኝ ከነበሩት ሚክ ማካርቲ ጋር ሊስማማ አልቻለም። ቢሆንም ችሎታውን ያስተዋሉት አሠልጣኝ ለ18 ወራት አስፈረሙት። ይህ የሆነው ከዛሬ ስድስት ዓመታት በፊት ነበር።

Image copyright CORSHAM TOWN

ፊርማውን ካኖረ ከስድስት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢፕስዊች ተሰለፈ። ከዚያ በኋላ ባሉት 18 ጨዋታዎችም ይህን ያህል የመሰለፍ ዕድል አላገኘም። የወቅቱ የክለብ ጓደኞቹ 'ለምን አልተሰልፍኩም?' ብሎ ከአሠልጣኞች ጋር ይጋጭ ነበር ይሉታል።

2015 ላይ ለቦርንመዝ ፈረመ፤ በ8 ሚሊዮን ፓውንድ። ነገር ግን የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ በገባ በ6 ደቂቃ ውስጥ ተጎድቶ ወጣ። ለ17 ወራትም ምንም ዓይነት ጨዋታ ማድረግ አልቻለም ነበር።

ይሄኔ ነው ቦርንመዝ ለአስቶን ቪላ አሳልፈው በውሰት የሰጠው። ቪላ ፕሪሚዬር ሊጉን እንዲቀላቀል ሚንግስ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ክለቡ በቋሚነት እንዲያስፈርመውም ሆነ።

ሚንግስ ለአንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን መጫወት እንደሚፈልግ እና ህልሙ እውን እንደሚሆንም በዙሪያው ላሉ ሰዎች ይነግራቸው ነበር። እነሆ ህልሙ እውን ሆኖ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተመርጧል። እንግሊዝ ዛሬ ምሽት ከኮሶቮ ጋር በምታደርገው ጨዋታም ይሰለፋል ተብሎ ይጠበቃል።

አልፈልግህም ያለው ሳውዝሃምፕተን በዚህ ዓመት በጣም ብዙ ጎል ተቆጥሮበታል። በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ 19ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት። ብዙዎች እንደው ሳውዝሃምፕተኖች ታይሮን ሚንግስን ቀጫጫ ነው ብለው ማሰናበታቸው ይቆጫቸው ይሆን? ሲሉ ይጠየቃሉ። ሚንግስ ግን ምንም ዓይነት ቁጭትም ቂምም የለበትም።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ