ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ሊወያዩ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ጋር ሊወያዩ ነው Image copyright EPRDF OFFICIAL

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግንባሩን በማዋሃድ ወጥ ፓርቲ ለመመስረት በቀረበለት የውህደት ዝርዝር ጥናት ላይ ተወያይቶ በስድስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ከስምምነት ላይ መድረሱን አሳውቋል።

በስብሰባው ላይ ከተሳተፉት የግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል የቀረበውን ሃሳብ ተቃውመው ድምጽ የሰጡት የህወሓት አባላት ሲሆኑ ከቀድሞው የደህንነት ተቋም ኃላፊ ከአቶ ጌታቸው አሰፋ በስተቀር የህወሓት አባላት መሳተፋቸውን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባል አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢሕአዴግ እዋሀዳለሁ ማለቱን የፖለቲካ ተንታኞች እንዴት ያዩታል?

ኢህአዴግን ያጣበቀው ሙጫ እየለቀቀ ይሆን?

ውሳኔው በተሰጠበት ጊዜ ስድስት ብቻ መቃወማቸው ድምጽ በሚሰጥበት ወቅት ከተሳታፊዎች መካከል "መውጣትና መግባት" ስለነበረ በአጋጣሚ የተፈጠረ መሆኑን አቶ አስመላሽ ገልጸው በውይይቱ ሁሉም እንደተሳተፉና "በፓርቲያቸው አቋም ጸንተው መውጣታቸውን" ገልጸዋል።

በዚህ ወሳኝ ድምጽ በሚሰጥበት ጊዜ ሁለቱ አባላት ያለመገኘታቸው አጠያያቂ ቢሆንም አቶ ስመላሽ በጉዳየ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የድርጅቱ ውህደትን በሚመለከቱ ቀጣይ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ዛሬም ስብሰባውን የቀጠለ ሲሆን ውህደትን በተመለከተ የቀረበውን ሃሳብ የተቃወሙት የህወሓት አባላት ግን በዛሬው ስብሰባ ላይ እንደማይሳተፉ አቶ አስመላሽ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ የት ናቸው? የእስር ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል?

የ31 ዓመቱ ኢሕአዴግ ማን ነው?

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ከህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር መገናኘት እንደሚፈልጉ በመግለጻቸው ከእርሳቸው ጋር እንደሚነጋገሩ አቶ አስመላሽ ጠቁመዋል።

ጨምረውም ህወሓት የኢህአዴግ ውህደትን በተመለከተ ከዚህ ቀደምም አቋሙን እንዳሳወቀ አስታውሰው ነገር ግን ሂደቱ ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ እስከ ድርጅቱ ጉባኤ ድረስ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የህወሓትን ቀጣይ ውሳኔ በተመለከተም "ከአሁን በኋላ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በፓርቲው አቋምና አላማ ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል" ያሉት አቶ አስመላሽ በህወሓት መጻኢ ዕድል ላይ "ከፓርቲው ውጪ ሌላ ኃይል መወሰን አይችልም" ብለዋል።

የውህደት እርምጃ ጅማሬ

ለወራት ሲያነጋግር በቆየው የገዢው ግንባር የኢህአዴግን አባልና አጋር ፓርቲዎችን በማዋሃድ አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ የመመስረት ሂደትን በተመለከተ የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኅዳር 06/2012 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ውሳኔ ላይ መድረሱን አሳውቋል።

አገሪቱን 30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሲመራ የቆየው ግንባሩ የአራት ክልላዊ ፓርቲዎች ኅብረት ሲሆን ለዓመታት ሲነሳና ሲተው የቆየውን አንድ ወጥ ውህድ ፓርቲ የመሆን ሂደትን ዕውን ለማድረግ ለወራት ሲሰራ መቆየቱን የተለያዩ የግንባሩ ባለስልጣናት ሲናገሩ ቆይተዋል።

በዚህ መሰረትም 36 አባላት ያሉት የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ "የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ" ተብሎ ይመሰረታል የተባለውን ድርጅት ዕውን ለማድረግ ያስችላል ተብሎ የቀረበለትን የውህደት ዝርዝር ጥናት ላይ ተወያይቶ በአብላጫ ድምፅ ስምምነት ላይ መድረሱን ይፋ አድርጓል።

ኢህአዴግ እዋሃዳለሁ ሲል የምሩን ነው?

"ኢህአዴግ ተዳክሟል ብላችሁ እንዳትሳሳቱ" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ይህንን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ የኢህአዴግ ውህደትን በተመለከተ የተደረገው ወሳኝ ስብሰሰባ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቅሰው "ውህደቱ የኢትዮጵያን የፌዴራል ሥርዓት ይበልጥ የሚያጠናክር፣ ተሰሚነት ላልነበራቸው አጋር ድርጅቶች እኩል ድምጽ የሚሰጥ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም ይህ እርምጃ "ኅብረ ብሔራዊነትን የሚያጸና፣ አካታችነትንና ፍትሃዊ ውክልናን የሚያረጋግጥ ሁነኛ አቅጣጫ ነው። የፓርቲው ውሕደት አገራዊ አንድነትን ከኅብረ ብሔራዊነት ጋር አስተሳስሮ ለመጓዝ ዕድል" እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባውን ባደረገበት ጊዜ ከአራቱ የግንባሩ አባላት በተጨማሪ አጋር የተባሉት የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአፋር ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄና የሐረሪ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ካለድምጽ ተሳትፈዋል።

ህወሓት: "እሳትና ጭድ የሆኑ ፓርቲዎች ሊዋሃዱ አይችሉም"

"ኢህአዴግ ነፃ ገበያም፣ ነፃ ፖለቲካም አላካሄደም" ፀደቀ ይሁኔ (ኢንጂነር )

የግንባሩን ውህደት በተመለከተ የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን በማስከተልም በስብሰባው ላይ የተገኙ የአራቱ የግንባሩ አባላት በቀረበው ሃሳብ ላይ ድምጽ ሰጥተው በስድስት ተቃውሞ በድምጽ ብልጫ ከውሳኔ ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

በሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ ላይ በሰባት አባላቱ የተወከለውና ቀደም ሲል ጀምሮ በውህደቱ ሂደት ላይ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ የነበረው የግንባሩ አንጋፋ መስራች የህወሓት ስድስት አባላት ውሳኔውን እንደተቃወሙት ተነግሯል። ሰባተኛው ተሳታፊ በውሳኔው ላይ የያዙት አቋም እስካሁን ምን እንደሆነ አልታወቀም።

ውህዱ ፓርቲ ምን ይዞ ይመጣል?

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ፍቃዱ ተሰማ ከውሳኔው በኋላ ለብሔራዊው ቴሌቪዥን በሰጡት ማብራሪያ በስብሰባው ላይ አሁን ስላለው ፌደራላዊ አስተዳደር፣ ቋንቋ፣ የብሔርና አገራዊ ማንነት፣ ፍትሃዊ ውክልናንና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በዝርዝር መወያየቱን ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት የአዲሱ ውህድ ፓርቲ ዋነኛ ምሰሶ የሚሆኑትን በአምስት ነጥቦች አስቀምጠውታል።

1. ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ይህም በፓርቲው ሕገ ደንብና ፕሮግራም ውስጥ እንደሚካተት።

2. የክልሎች እራስን በራስ የማስተዳደርና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደሚከበር።

3. አጋር ድርጅቶችን ጨምሮ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያካተተና ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖራቸው እንደሚደረግ።

4. የብሔር ማንነትና አገራዊ አንድነት ተጠናክሮ ለማስቀጠል ብሔራዊ ማንነትና አገራዊ አንድነትን አስማምቶ የአገሪቱ ፖለቲካ መምራት።

5. የቋንቋ ብዝሐነትን በመቀበል ተጨማሪ የሥራ ቋንቋን በፓርቲ ደረጃ

ቀጣዩ ውሳኔ ከማን ይጠበቃል?

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የግንባሩን ውህደት በተመለከተ ጉዳዩ እዚሁ ላይ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በዓመት ሁለት ጊዜ ለሚካሄደው የድርጅቱ ምክር ቤት ይቀርባል። ምክር ቤቱ ከአራቱ ድርጅቶች የተወጣጡ 180 አባላት ያሉት ሲሆን ቁልፍ የሚባለው ውሳኔን የመስጠት ስልጣን አለው።

ይህ ሂደት በመጨረሻም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአራቱም ድርጅቶች ተወካዮች ለሚመክሩበት የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ይቀርብና የውህደቱ ጉዳይ የመጨረሻውን መቋጫ ሲያገኝ አገር አቀፉ ውህድ ፓርቲ አውን ይሆናል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ