የሲዳማ ሕዝበ-ውሳኔ፡ አዲስ ክልል፤ አዲስ ፈተና?

People queuing to vote Image copyright AFP

የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች ዛሬ [ኅዳር 10/2012] ሕዝበ-ውሳኔ ላይ ናቸው። ሲዳማ ራሱን የቻለ ክልል ይሁን ወይስ በደቡብ ክልል ውስጥ ይቀጥል የሚለውን ለመለየት።

ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሕዝበ-ውሳኔው ለመሳተፍ ተመዝግበዋል። ጎጆ ለደቡብ፤ ሻፌታ ለሲዳማ ምልክት ሆነውም ቀርበዋል።

ድምፅ መስጠት የሚጀመረው ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ነው ቢባልም መራጮች ወደ ጣብያዎች ማምራት የጀመሩት ከንጋቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ነው።

የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች በሕዝበ ውሳኔ እየተሳተፉ ነው

የደቡብ ክልል ዋና ከተማ የሆነችው ሐዋሳም ዛሬ ድምፅ ለመስጠት በወጡ እና ረዥሙ ሰልፍ ሳይበግራቸው በሚጠባበቁ ሰዎች ተሞልታለች።

አሁን ለምን?

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሚያዚያ 2010 ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በርካታ ፖለቲካዊ ለውጦችን አከናውነዋል።

በተነፃፃሪ ዝግ ሃገር እየተባለች የምትወቀሰው ኢትዮጵያ ወደ አንፃራዊ ዴሞክራሲ እና ነፃነት እንደመጣች ብዙዎች ያምናሉ። አልፎም ለሁለት አስርታት ተኮራርፈው የነበሩት የኢትዮጵያ እና ኤርትራን መንግሥታት እርቅ ያወረዱት በጠ/ሚ አብይ ዘመን ነው። ለዚህም ተግባራቸው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆን ችለዋል።

ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንገድ አልጋ ባልጋ አልነበረም። ድኅረ-አብይ ያለው ጊዜ ብሔር ተኮር ግጭቶች በየቦታው የተስተዋሉበትና ሰላም የራቃቸው አካባቢዎች የበረከቱበት ነው። ሰውዬው ሰላምን በማስከበር ረገድ ላላ ያለ አቋም ነው ያላቸው ተብለውም ይተቻሉ።

ባለፉት 20 ወራት በተለያዩ ቦታዎች ብሔርን አስታከው በተከሰቱ ግጭቶች ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንደተፈናቀሉ ይታመናል።

ሲዳማ ዞንም ከሌሎች የተለየች አልነበረችም። ሲዳማ ክልል መሆን አለባት የሚለው ጥያቄ ጎልቶ መሰማት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም ሕዝበ-ውሳኔው ሐምሌ ላይ መካሄድ አለበት ያሉ ሰልፈኞች ከሌሎች የዞኑ ነዋሪዎች ጋር ተጋጭተው ሕይወት መጥፋቱ፤ ንብረት መውደሙም የሚታወስ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮምኛና ሌሎችም ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ወሰነ

'ኤጄቶ' የተሰኘው ሲዳማ ክልል መሆን አለባት አቀንቃኝ የወጣቶች ክንፍ በወቅቱ ጥፋት አድርሷል ተብሎ ተወቅሶ ነበር። በዚህ ግጭት ቢያንስ 25 ሰዎች ሞታቸው ተዘግቧል።

የሲዳማ ክልል አቀንቃኞች አመክንዮ

ከኢህአዴግ ዘመነ-መንግሥት የነበረው ሕገ-መንግሥት ሲዳማን ክፍለ-ሃገር ሲል ይጠራት ነበር። ውልደቱ 1987 ዓ.ም. የሆነው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ዘጠኝ ክልሎች አሉት። አዲስ አበባና እና ድሬዳዋ ደግሞ የከተማ አስተዳደሮች ናቸው። ሕገ-መንግሥቱ ክልላቱን የከፋፈለው ብሔርን መሠረት አድርጎ ነው።

ነገር ግን የሲዳማ ብሔር ከሌሎች ከ50 በላይ ብሔሮች ጋር በደቡብ ክልል ውስጥ እንዲካተት ሆነ። የሲዳማ ሕዝብ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ 4 በመቶ እንደሆነ ይታመናል። አምስተኛው ትልቁ ብሔርም ነው። ተንታኞች ይህ እውነታ ሲዳማ ክልል ትሁን ለሚለው ሃሳብ ትልቅ ማሳመኛ ነው ይላሉ።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ፡ የሐዋሳ ነዋሪዎች ምን ይላሉ

ሲዳማ ክልል እንድትሆን ሕዝበ-ውሳኔው የሚበይን ከሆነ የሲዳማ ክልል 10ኛው ሆኖ ይመዘገባል። አልፎም የራሱን ሕገ መንግሥት ማውጣት እና የፖሊስ ኃይል ማቋቋምም ይችላል።

ከዚያ ባለፈም የራሱ በጀት የሚመደብለት ይሆናል። የሲዳማ ክልል ትሁን አቀንቃኞች የቋንቋና የባሕል ዕድገት ሌላኛው ክልል የመሆን ጥቅም ነው ሲሉ ያብራራሉ።

አዲስ ክልል. . . አዲስ ፈተና?

ምንም እንኳ ሲዳማ ክልል መሆን አለባት የሚለውን ሃሳብ ተቃውመው አደባባይ የወጡ ባይኖሩም፣ ሲዳማ ክልል ከሆነች ሌሎችም ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ ብለው የሚሰጉ አሉ።

ለምሳሌ ደቡብ ክልል ውስጥ ብቻ እንኳ የወላይታ እና ሃዲያ ሕዝቦች ክልል የመሆን ጥያቄን ማነሳሳት ከጀመሩ ውለው አድረዋል።

ይህ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር አዲስ ፈተና ይዞ ሊመጣ ይችላል ተብሎ ይገመታል። የክልል እንሁን ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም ማለት ደግሞ ብሔር ተኮር ውጥረቶች ይጨምራሉ እንጂ አይቀንስም ነው ዋነኛው መከራከሪያ።

ህወሓት፡ ሃገራዊ ምርጫ የሚራዘም ከሆነ ትግራይ የራሷን ምርጫ ታካሂዳለች

የሲዳማ ሕዝበ-ውሳኔ ዞን ውስጥ ያለውን ብሔር ተኮር ውጥረት ያረግበው ይሆን? ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።

ሌላው ቢቀር እንኳ ሕዝበ-ውሳኔው ለቀጣይ ሃገር አቀፍ ምርጫ መሞከሪያ ይሆናልና በጎ ጎኑ ያመዝናል የሚሉ ድምፆች ይሰማሉ።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የምርጫ ጣቢያ ሠራተኞች የአመራጥ ሂደቱን ለድምፅ ሰጭዎች የማስረዳት ኃላፊነት አለባቸው

በምርጫው እነማን ይሳተፋሉ?

በሕዝበ-ውሳኔው ለመሳተፍ ቢያንስ ላለፉት ስድስት ወራት ሲዳማ ዞን ውስጥ ነዋሪ መሆንን የሚያሳይ መታወቂያ መያዝ ይጠበቃል።

የምርጫ ወረቀቱ ላይ ሁለት ምልክቶች ይገኛሉ። አንደኛው ጎጆ፤ ሌላኛው ደግሞ የሲዳማ ብሔር ባህላዊ ዕቃ ሻፌታ ነው። ሻፌታ ብለው የሚመርጡ ሲዳማ ክልል እንድትሆን ድምፃቸውን ሰጥተዋል ማለት ነው። ጎጆ መራጮች ደግሞ ሲዳማ ዞን በድቡብ ክልል ውስጥ እንድትቀጥል የሚሹ ናቸው።

የምርጫው ውጤት ነገ ዕለተ ሐሙስ አሊያም አርብ እንደሚታወቅ የምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ