በምዕራብ ወለጋ ዞን የኦሮሚያ የመንግሥት ኃላፊ በታጣቂዎች ተገደሉ

አቶ ቶላ ገዳ Image copyright ODP
አጭር የምስል መግለጫ አቶ ቶላ ገዳ ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ ሕይወታቸው ማለፉ ተነግሯል

በምዕራብ ወለጋ ዞን አንድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባለስልጣን መንገድ ላይ በታጣቂዎች በተከፈተባቸው ተኩስ ተገደሉ።

ትናንት [ረቡዕ] በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ውስጥ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ቶላ ገዳ ለሥራ ጉዳይ ወደ ምዕራብ ወለጋ ቄለም ወለጋ ዞን እየሄዱ ባሉበት ወቅት፣ ላሎ አሳቢ ተብሎ በሚታወቀው ወረዳ ውስጥ እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን ቢቢሲ አረጋግጧል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ኤሊያስ ኡመታ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህ ግድያ የተፈጸመው ላሎ አሳቢ ወረዳ ውስጥ ጋራ ቶሬ በሚባል ቦታ ላይ ረቡዕ ዕለት ጠዋት አምስት ሰዓት አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የደምቢ ዶሎ ከንቲባ በጥይት ተመትተው ቆሰሉ

ኢትዮጵያዊያን፣ ጃፓናዊትና ህንዳዊ በታጣቂዎች ተገደሉ

አስተዳዳሪው ጨምረው እንደተናገሩት አቶ ቶላን የገደሉት ታጣቂዎች እየተጓዙበት በነበረው መኪና ላይ ከግራና ከቀኝ ሆነው በከፈቱት ተኩስ በመኪናው ውስጥ እየተጓዙ የነበሩ መንገደኞችን ኢላማ አድርገው እንደሆነ አመልክተዋል።

በታጣቂዎቹ ጥቃት የተገደሉት አቶ ቶላ ገዳ የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር የመንገዶች ባለስልጣን ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ እንደሆኑ አስተዳዳሪው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ከአቶ ቶላ ጋር ለሥራ ጉዳይ ሌሎች ሰዎች በመኪናው ውስጥ የነበሩ ሲሆን ከእነርሱም መካከል፤ በመኪናው ውስጥ የቄለም ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ከጸጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤትም ሌሎች ሰዎች አብረዋቸው ነበሩ።

በተጨማሪም የጸጥታ አካላትም በመኪናው ውስጥ ከተጓዦቹ ጋር የነበሩ ሲሆን ጥቃቱ በተፈጸመበት ቅጽበት ፈጻሚዎቹን ለመያዝ ለመከተል ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው እንደቀረም ተነግሯል።

በምሥራቅ ወለጋ ሁለት ሰዎች ተገደሉ

ከተገደሉት አንዱ የማዕድን ኩባንያው ባለቤት ነበር

ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ የአቶ ቶላን ሕይወት ለህልፈት የዳረገው ጥይት በመኪናው የፊት መስታወት በኩል የተተኮሰ ሲሆን፤ አቶ ቶላ በጥይት እንደተመቱ ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ ወዲያውኑ ሕይወታቸው ማለፉን አስተዳዳሪው ገጸዋል።

በተሽከርካሪው ላይ በታጣቂዎች በተከፈተው ተኩስ ከአቶ ቶላ ውጪ አብረዋቸው ይጓዙ በነበሩት ሰዎች ላይ ግን ምንም ጉዳት ሳይርስባቸው ሊተርፉ ችለዋል ተብሏል።

አቶ ቶላ ገዳ በጥቃቱ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ አስከሬናቸውም በአቅራቢያው ወደሚገኘው የአይራ ሆስፒታል እንደተላከና በኋላም ወደ ቤተሰቦቻቸው መሸኘቱን አስተዳዳሪው አቶ ኤሊያስ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ይህ ጥቃት በማን እንደተፈጸመ በአሁኑ ወቅት የታወቀ ነገር እንደሌለ የተነገረ ሲሆን ሲሆን በአካባቢው ያሉ የጸጥታ አካላት በክስተቱ ፈጻሚዎች ዙሪያ ክትትልና ምርመራ እያደረጉ ስለሆነ ከምርመራው የሚገኘው ውጤት በወቅቱ ይፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ የጉሊሶ ከተማ ከንቲባ ግድያ የነዋሪውን ስጋት አባብሷል

በምዕራብ ወለጋ መንዲ በመከላከያ ካምፕ ላይ የተወረወረ ቦምብ አንድ ሰው ገደለ

በአቶ ቶላና በባልደረቦቻቸው መኪና ላይ ጥቃት በተፈጸመበት ስፍራ ላይ የሰዎች ሕይወት አይጥፋ እንጂ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ድርጊት የተፈጸመበት መሆኑንም አቶ ኤሊያስ ጠቅሰዋል።

በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በምዕራብ ወለጋና በቄለም ወለጋ ዞኖች ውስጥ የመንግሥት ባለስልጣናትን ኢላማ ያደረጉ ግድያና ጥቃቶች በተደጋጋሚ ሲፈጸም የቆየ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሰራተኞችና በተለያዩ የግል ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከተለያዩ አካላት የተዋቀረ ኮማንድ ፖስት የአካባቢውን ጸጥታ ለማስጠበቅ ጥረት እያደረገ ሲሆን ነዋሪዎችም በተደጋጋሚ ስላለው የጸጥታ ስጋትና ችግር ቅሬታ ሲያርቡ ቆይተዋል።

አንዳንድ ወገኖች በአካባቢው ለሚፈጸመው ጥቃት ከኦነግ ተለይቶ የወጣውና ኦነግ ሸኔ ተብሎ የሚጠራውን ቡድን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ