የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡጁምቡራ በአሸባሪነት በተጠረጠረ ግለሰብ ችግር ገጠመው

በቡጁምቡራ ያረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን Image copyright Burundi security Twitter page
አጭር የምስል መግለጫ በቡጁምቡራ ያረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

ዛሬ ከሰዓት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ቡጁምቡራ ውስጥ ካረፈ በኋላ በሽብር ድርጊት የተጠረጠረ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የቡሩንዲ ባለስልጣናት አረጋገጡ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን አንድ ተሳፋሪ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ገብቶ በመዝጋት በሰነዘረው ማስፈራሪያ አውሮፕላኑ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ወደሚያርፉበት የቡጁምቡራ አየር ማረፊያ እንዲቆም መደረጉም ተነግሯል።

አውሮፕላኑ ዛሬ በቀጥታ በረራ ከአዲስ አበባ ወደ ቡሩንዲ ዋና ከተማ ቡጁምቡራ እየበረረ ሳለ ነበር ችግሩ የተከሰተው ተብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የበረራ ቁጥር ኢቲ817 ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ቡጁምቡራ እና ኪጋሊ ሲበር በነበረው አውሮፕላን ውስጥ የነበረ ተሳፋሪ አውሮፕላኑ ቡጁምቡራ ላይ ሊያርፍ ሲል በውሸት ቦምብ ይዣለሁ ብሎ ማስፈራራቱን ተከትሎ አለመረጋጋት ተፈጥሮ ነበር ብሏል።

አውሮፕላኑ በሰላም ያረፈ ሲሆን ተሳፋሪዎችም ቢሆኑ በተለመደው መልኩ ከአውሮፕላኑ መውረድ ችለዋል ይላል መግለጫው።

ፖሊስም ግለሰቡን በዓለማቀፍ የአየር በረራ ረብሻ መሰረት በቁጥጥር ስር አውሎታል።

አውሮላኑ እና የበረራ ሰራተኞቹ ወደታቀደላቸው ቀጣይ በረራ መቀጠላቸውንም አየር መንገዱ ያወጣው መግለጫ ይገልጻል።

በበራው ላይ የነበሩ ሰራተኞች እንዲሁም የቡጁምቡራ እና የቡሩንዲ የደህንነት ቡድኖች ላሳዩት የተቀናጀ የደህንነት ተግባርም ሊመሰገኑ ይገባል ብሏል የኢትዮጵያ አየር መንገድ።

በመጨረሻም በበረራ ቁጥር ኢቲ817 ተሳፍረው ለነበሩ ደንበⶉች ላጋጠማቸው ማንኛውም አይነት መጉላላት አየር መንገዱ ይቅርታ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፊቱን ወደ ቻይና እያዞረ ይሆን?

ቦይንግ ለተጎጂ ቤተሰቦች 100ሚ. ዶላር ሊሰጥ ነው

ቢቢሲ ስማቸው እንዳይጠቀስ ከጠየቁ የአየር መንገዱ ሰራተኛ ለማረጋገጥ እንደቻለው የተባለው ችግር እንዳጋጠመና ምንም ጉዳት ሳይደርስ ቡጁምቡራ አርፏል።

ነገር ግን መረጃ የተጠየቁት የአየር ባልደረባ ስለክስተቱ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበው ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ለመስጠት አልፈቀዱም።

ክስተቱን በተመለከተ ለቢቢሲ ያረጋገጡት የአየር መንገዱ ባልደረባ እንደሚሉት ከሆነ "አውሮፕላኑ በአየር ማረፊያው ወታደራዊ ክፍል ውስጥ እንዲያርፍ ተደርጎ ችግሩን የፈጠረው ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውሏል።"

ነገር ግን በአውሮፕላኑ ውስጥ ያጋጠመውን ችግር የፈጠረው ግለሰብ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ግለሰቡ ፈንጂ መያዙን በመግለጽ አውሮፕላኑን እንደሚያፈነዳው ባስፈራራበት ወቅት ከፍተኛ ፍርሃት በተሳፋሪዎቹ ዘንድ መፈጠሩን ቢቢሲ ያነጋገራቸው መንገደኞች ገልጸዋል።

የቡሩንዲ የደህንት ሚኒስቴር በትዊተር ገጹ ላይ ክስተቱን አረጋግጦ "በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ተሳፍሮ የነበረ ተጠርጣሪ ሽብርተኛ ቡጁምቡራ አየር ማረፊያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውሏል" ብሏል።

ክስተቱን በተመለከተ ቢቢሲ ያገኘውና እስካሁን በሁለተኛ ወገን ያልተረጋገጠው መረጃ እንደሚያመለክተው ግለሰቡ በአውሮፕላኑ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ገብቶ በመዝጋት አውሮፕላኑን እንደሚያፈነዳው በመግለጽ በማስፈራራቱ ችግሩ መከሰቱ አመልክቷል።

ከዚህ አንጻር ለቢቢሲ የተናገሩት የአየር መንገዱ ባልደረባ ክስተቱ በሰላም መጠናቀቁንና በተሳፋሪዎችም ሆነ በአውሮፕላኑ ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱን ገልጸዋል።

በእርግጥ ግለሰቡ እንዳለው የሚፈነዳ ነገር ይዞ እንደነበረ የሚያመለክት ነገር ያልተገኘ ሲሆን፤ ለፈጸመው ድርጊትም ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን ምንም የታወቀ ነገር የለም።

አውሮፕላኑ ምን ያህል ተጓዦችን አሳፍሮ እንደነበረና ችግሩ የተከሰተው ለማረፍ በተቃረበበት ይሁን ወይም በጉዞ ላይ እንዳለ አልታወቀም።

ክስተቱን ተከትሎ አውሮፕላኑ በአየር ማረፊያው ውስጥ በሚገኝ የወታደራዊ አውሮፕላኖች ማቆሚያ ክፍል እንዲቆይ እንደተደረገ ምንጮች ከቡጁምቡራ አመልክተዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ