ዴሞክራቲክ ኮንጎ፡ በኩፍኝ ወረርሽኝ 5000 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ

የኩፍኝ ክትባት Image copyright AFP/Getty

በፈረንጆቹ 2019 በዴሞክራቲክ ኮንጎ ያጋጠመውና በመላ አገሪቱ የተዛመተው የኩፍኝ ወረርሽኝ 5 ሺ የሚደርሱ ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ገለጹ።

250 መቶ ሺ የሚደርሱ ዜጎች ደግሞ በዚሁ ዓመት በበሽታው መያዛቸው ታውቋል።

ክትባት ከየት ተነስቶ የት ደረሰ?

አለማችን የኩፍኝ ወረርሽኝ እንደሚያሰጋት አለም አቀፉ ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው በዴሞክራቲክ ኮንጎ ያጋጠመው ወረርሽኝ በዓለማችን ፈጣኑ ወረርሽኝ ነው። ኩፍኝ፤ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ኢቦላ ባለፉት 15 ወራት ከገደላቸው ሰዎች ሁለት እጥፍ የሚሆኑ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል።

የአገሪቱ መንግሥት የዓለማቀፉ የጤና ድርጅት መስከረም ላይ በጀመሩት የድንገተኛ የክትባት ፕሮግራም እስከ 8 መቶ ሺ የሚደርሱ ህጻናትን ለመከተብ ታስቦ ነበር።

ነገር ግን ደካማ የሆነ የመሰረተ ልማት፣ አለመረጋጋትና በቂ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ባለመኖራቸው ምክንያት የክትባት ስራው የታሰበለትን ያህል ውጤታማ መሆን ሳይችል ቀርቷል።

እስካሁን 4 ሚሊየን የሚደርሱ ህጻናት የኩፍኝ ክትባት የተሰጣቸው ሲሆን፤ ባለሙያዎች ግን ክትባቱን ያገኙት ከአገሪቱ ህዝብ ከግማሽ በታች የሚሆኑት ናቸው ብለዋል። ስለዚህም በቂ ክትባት ባለመኖሩና በተለያዩ ምክንያቶች ክትባቱ ወደ ዜጎች መድረስ ባለመቻሉ ወረርሽኙን መቆጣጠር ከባድ ሊሆን እንመዲችል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

እስካሁን በተሰበሰበ መረጃ መሰረት በዴሞክራቲክ ኮንጎ በኩፍኝ ከተያዙ ዜጎች መካከል አብዛናዎቹ ጨቅላ ህጻናት ናቸው።

ኩፍኝ ምንድነው?

ኩፍኝ በቫይረስ የሚተላላፍ በሸታ ሲሆን ከሰው ወደ ሰው በከፍተኛ ሁኔታ የሚተላለፍ በሽታ ነው። በወቅቱ ካልታከመም የአይን ብርሃንን እስከማጣት ሊያደርስ፣ ለሳንባ ምች፣ ለአንጎል እብጠትና ለኢንፌክሽን ያጋልጣል።

ኢትዮጵያዊያን ለክትባቶች ከፍተኛ የሆነ አውንታዊ አመለካከት አላቸው

በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ሽፍታ፣ የዓይን ቀይ መሆን፣ የአፍንጫ ፈሳሽና አንዳንዴ የሚከሰት ሳል የበሽታው የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች ናቸው።

በኩፍኝ የተያዘ ሰው በቶሎ ህክምና ካላገኘ በሽታው ከጀመረበት አንስቶ ባሉ ጥቂት ቀናት ውስት የሚያስከትላቸው ጉዳቶች ሲኖሩ ከረጅም ዓመታት በኋላ የሚያስከትላውም ጉዳቶች አሉ።

ለዚህ በሽታ ዋነኛ የመተላላፊያ መንገዶች በትንፋሽ እና ንክኪ ናቸው።

የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በሁሉም የአለማችን ሀገራት በ2016 ከታየው በ2017 ሰላሳ በመቶ ጨምሯል። ባለሙያዎች ለቁጥሩ መጨመር እንደምክንያት ያነሱት ስለ ክትባቱ ያለው የተሳሳተ መረጃንና የህክምና አገልግሎት ስርአቶች መውደቅን ነው።

በየዓመቱም በመላው ዓለም 110 ሺ የሚሆኑ ሰዎች በኩፍኝ በሽታ ህይወታቸው ያልፋል።