#5 እሷ ማናት?፡ የምሥራቅ አፍሪካ ማይክሮሶፍት ቢሮን የምትመራው ወጣት ኢትዮጵያዊት

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የአፍሪካን የማይክሮ ሶፍት ገቤያ እንድታሳልጥ የተመረጠችው ኢትዮጵያዊት እንስት

አምሮቴ አብደላ እባላለሁ፤ ኑሮዬን በኬንያ መዲና በናይሮቢ ካደረኩኝ ከ6 ዓመታት በላይ ሆኖኛል። ግማሽ ኢትዯጵያዊት እና ግማሽ ኤርትራዊት ስሆን በእናቴ ክርስቲያንና በአባቴ ደግሞ ሙስሊም ነኝ።

በ33 ዓመቴ ነበር የምሥራቅ አፍሪካ ዋና ኃላፊ እንድሆን የተመደብኩት። በጣም ነበር ውሳኔው የገረመኝ። አሁን አለቃ ሆኜ የ33 ዓመት ወጣት፣ አምሮቴን፣ የምቀጥራት አይመስለኝም።

ለቅጥር የተጠራሁ ዕለት አዲሱን አለቃዬን "ግን ታውቃለህ 'ኮድ' ማድረግ አልችልም" ስለው አይረሳኝም፤ እርሱም "አውቃለሁ 'ኮድ' ማድረግ የሚችሉ በ100 ሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች አሉኝ። አንቺ ደግሞ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን ወደ አፍሪካ ማምጣትና ማስፋፋት የምንችልባቸውን መንገዶች ታዋቅሪልናለሽ" ብሎኝ ይኸው እስከዛሬ አለኹኝ።

አሁን በቴክኖሎጂ ዓለም ውስጥ ተሰማርቻለሁ ስል አፌን ሞልቼ ነው።

በሥራ ገበታ ላይ ሴት መሆን ለእኔ ከችግሩ ይልቅ ጥሩ ጎኖቹ ይበዛሉ ባይ ነኝ። ለምን ብባል? ሴት መሆን በራሱ የሌሎችን ስሜትም ሆነ ሁኔታዎችን ለመረዳት የሚያስፈልገን ብስለት አለን ብዬ አምናለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ሥራ ላይ ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮችንና እንቅፋቶችን የምናይበት መንገድ ለየት በማለቱ መፍትሔ ለመዘየድ ጊዜ አይፈጅብንም ።

ለአፍሪካ ያለኝ ቦታ በጣም ጥልቅ ነው። ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአፍሪካን ዕድገት ማፋጠን የምንችልባቸውን መንገዶችና ሌሎች በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎችን ለማሳደግ ነው የምሠራው።

Image copyright MICROSOFT

ኃላፊ ወይም አለቃ ሲባል ብዙ ጊዜ ከስያሜው በስተጀርባ ሌሎች ነገሮች መኖራቸውን እንረሳለን። የተማርኩት ነገር ቢኖር የተለያዩ ሰዎችን ማስተዳደርን ምክንያቱም ከእኔ ሥር ሆነው ከሚሠሩት መካከል ታላለቆቼም ታናናሾቼም ነበሩበት።

የቴክኖሎጂ ሰው ባለመሆኔም ደግሞ ከእኔ በላይ የሚያውቁ ሰዎች አይጠፉም ነበር። ስለዚህ አቅምን ማወቅ እና ከዚያም በላይ ደግሞ የምናውቃቸውንና የማናውቃቸውን ነገሮች መለየት በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ሁልጊዜ ራሳችንን ለመማር ማዘጋጀት አለብን።

ኃላፊ መሆን ማለት ደግሞ ስሙ ብቻ ሳይሆን በሰዎች ዘንድ ምን ያህል ተደማጭነት እንዳለን ጭምር ነው የሚወስነው። የኃላፊነት ቦታ ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ለራሳቸው ከሚሰጡት ቦታ ተነስቶ በሦስት የተለያዩ የአስተሳሰብ ዓይነቶች ያልፋሉ ።

በመጀመሪያ "ይህ ቦታዬ ነው? እዚህ ምንም ጥቅም የለኝም" በማለት ችሎታችንን የምንጠራጠርበት ሲሆን የሚቀጥለው ደግሞ በዚያ የሥራ ቦታ ላይ "እንደእኔ አስፈላጊ የለም" የሚል ስሜት ውስጥ እንገባለን።

ለሥራውም ለራሳችንም ጠቃሚ የሚሆነው ቀጥሎ ያለው የእድገት ደረጃ ሲሆን እሱም "ከእኔ ሥራው ይበልጣል። ከእኔ የተሻሉ፣ ፈጣን ጎበዝ ሰዎችን አምጥቼ ያስጀመርኩትን ሥራ ተቀብሎ በጥሩ መንገድ እንዲያልቅ ማድረግ አለብኝ" የምንልበት ነው።

ሴት መሆን በሥራ ዓለም ውስጥ ከባድ እንደሚሆን መገመት አያቅትም። ወንድ በበዛበት የሥራ ዘርፍ ውስጥ ሴት አለቃ መሆን አንዳንዴ ያስቸግራል። የማይረሳኝ ገጠመኝ የተቀጠርኩኝ ሰሞን ከመንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳጠናክር ተጠይቄ ለስብሰባ የሚኒስትር ቢሮ የሄድኩበትን ጊዜ ነው።

ወደ ስብሰባው ክፍል ስገባ ስንፃፃፍ የነበሩት ሚኒስትሩና የሥራ አጋሮቻቸው ቆመው በር በሩን ይመለከቱ ነበር።

ከተቀመጥኩም በኋላ እነሱ ቆመው በር በሩን ሲመለከቱ ግራ ገብቶኝ "ሌላ የምንጠብቀው ሰው አለ?" ብዬ ጠየኳቸው። መልሳቸው እስከዛሬ ያስቀኛል ... "አቶ አብደላን እየጠበቅን ነው" ሲሉኝ እኔም "አቶ አብደላ አባቴ ናቸው እርሳቸውን የምንጠብቅን ከሆነ ኢትዮጵያ ስለሆኑ ብዙ ልንጠብቅ ስለሚሆን ስብሰባውን መጀመር እንችላለን" አልኳቸው፤ በአንዴ ፊታቸው ሲለዋወጥ ትዝ ይለኛል።

ሴት መሆን ብቻ ሳይሆን የኃላፊነት ቦታ ያላት ወጣት ሴት መሆን ብዙውን ጊዜ ከባድ ነው። ሲያዩኝ ለማመን ይከብዳቸዋል፤ ሥራ ላይ እስኪያውቁኝም በችሎታዬ ለመተማመን ያስቸግራቸዋል። ከችግሩ የበለጠ ግን የሚከፈቱልኝ አጋጣሚዎች ይበዛሉ።

አሁን ደግሞ እንደ እኔ ኃላፊነት ተሸክመው ሥራ የሚሠሩ ሴትም ሆኑ ወንዶች ለሚመጣው ትውልድ ቦታውን ማመቻቸት አለብን ብዬ አምናለሁ። ጊዜው ስለሚቀያየር ለውጥም መምጣቱ ስለማይቀር አብረን መሄድ መቻል አለብን ብዬ አምናለሁ።

Image copyright MICROSOFT

ብዙ ሰዎች በሥራ ገበታ ላይ ሴቶች ለሌሎች ሴቶች ይከፋሉ ይላሉ። እኔ ግን አላምንበትም፤ ምክንያቱም ሁላችንም የተለያየ ፀባይ ነው ያለናን፤ ስለዚህ ይህ ጉዳይ ከፆታ ጋር ይገናኛል ብዬ አላስብም።

አንድ ሰው ጥሩ ከሆነ ወንድም ሆነ ሴት ጥሩ ሰው ነው፤ ክፉም ከሆነ እንደዚያው እንጂ ጠቅልለን ሁሉንም በአንድ ዕይታ መፈረጅ የለብንም ብዬ አስባለሁ።

ሰው ይሳሳታል ስለዚህ እኔም ሰው በመሆኔ ከጥፋት ነፃ ልሆን አልችልም። ቢሆንም ግን ማንኛውንም ስህተት ተብሎ የሚፈረጅን ነገር እንደ ጥፋት አልመለከተውም፤ ምክንያቱም የሆነ ነገር አስተምሮኝ እንደሚያልፍ አምናለሁ።

ከዚያም በላይ ደግሞ በጊዜው የወሰንኩት በወቅቱ በነበረኝ እውቀትና ዕይታ አንጻር በመሆኑ በዚያን ሰዓት ስህተት አልነበረም ብዬ አምናለሁ። በዚህ ሥራ መጀመሪያ ላይ ስሰማራ ለነበርኩት ወጣቷ አምሮቴም ይህንኑ ነው የምመክራት።

"አትፍሪ፣ ደፋር ሁኚ ደግሞም በውሳኔዎችሽ አትጠራጠሪ።"

ለወጣት ሴቶች ምክር ብሰጥ የምላቸው ለራሴ ከምስጠው ምክር ብዙም አይለይም። ለማድረግ ወይም ለማሳካት የሚያልሙት ነገር ካለ ከመሞከር ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም።

የምንፈልገውን ነገር ካልጠየቅንና በራሳችን ጥረን ለማግኘት ካልተሯሯጥን ማንም ምኞታችንን ለማሳካት አይሯሯጥልንም። ለዚህም ነው ሁልጊዜ በሙሉ አቅምና ፍላጎት ሞክሩ የምለው።

እሷ ማናት? የሚለው ጥንቅራችን ያሰቡበትን ዓላማ ለማሳካት ብዙ ውጣውረዶችን ያሳለፉ ሴቶችን ታሪክ የምናስቃኝበት ነው።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ