የአሜሪካና የቻይና እሰጣገባ ኢንተርኔትን ለሁለት እየከፈለው ይሆን?

ስልኳን የምትመለከት ሴት Image copyright Getty Images

ቻይናውያን የተቀረው ዓለም እንደ ልቡ ኢንተርኔትን በርብሮ የሚያገኛቸውን መረጃዎች ማግኘት አይችሉም። ለምሳሌ አንድ ቻይናዊ በጉግል መፈለጊያ ላይ ገብቶ ቻይና ብሎ ቢጽፍ የሚያገኘው መረጃ የተቀረው ዓለም ከሚያገኘው በእጅጉ የተለየ ነው።

የዓለማችን ከፍተኛው የህዝብ ቁጥር የምትይዘው ቻይና ኢንተርኔት በእጅጉ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ሀገራት የመጀመሪያውን ረድፍ ትይዛለች።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ደግሞ በቅርቡ ኢንተርኔት ለሁለት ይከፈላል፤ በቻይና የሚመራውና በአሜሪካ የሚመራው ተብሎ።

ሁሉንም በደህንነት ካሜራ የምትመለከተው ቻይና

ኢትዮ ቴሌኮም... ወዴት? ወዴት?

ይህንን ሀሳብ ባለፈው ዓመት ወደፊት ያመጡት የጉግል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤሪክ ሽሚት ናቸው።

የቻይና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መንግሥት እንዲያዩት የሚፈቅድላቸውን መረጃዎች ብቻ ነው መመልከት የሚችሉት፤ ለምሳሌም እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ድሮፕቦክስ ወይንም ፒንትረስት ያሉ የማህበራዊ ሚዲያዎችና መገልገያዎችን መጠቀምም አይችሉም።

በታይናንሜን አደባባይ ስለተፈጸመው ጭፍጨፋም ሆነ ማንኛውም ስለ ፕሬዚዳንታቸው ሺ ዢን ፒንግ የተሰጡ ትችቶችን በኢንተርኔት ላይ ፈልገው መመልከት አይችሉም።

ምንም እንኳን ቻይና በዓለማችን ትልቁን የህዝብ ቁጥር ብትይዝም ትልልቅ የሚባሉ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ መስራት ባለመቻላቸውና መረጃ እንደ ልብ መቀያየር ባለመቻሉ ምክንያት ቻይናን ለቅቀው መሄድ እየመረጡ ነው።

ሌላው ቀርቶ ወደ ቻይና ገበያዎች መግባት የሚፈልጉ ድርጅቶች ኢንተርኔት የተገደበ በመሆኑና ደንበኞቻቸውን እንደልብ ማግኘት ስለማይችሉ ወደ ሌሎች ሃገራት መሄድን ይመርጣሉ።

ግዙፉ አፕል እንኳን እ.አ.አ. በ2017 ለቻይና ገበያ ከሚያቀርባቸው ስልኮች ላይ 'የኒውዮርክ ታይምስ' እና 'ስካይፕ' መተግበሪያዎችን እንዲያጠፋ ቀጭን ትእዛዝ ተሰትቶት ነበር።

የአሜሪካው ስልክ አምራች ኩባንያም ሳያቅማማ ትእዛዙን ፈጽሟል።

'ሊንክድኢን' የተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ መገልገያ በመላው ዓለም የሚገኙ ስራ ፈላጊዎችንና እና ቀጣሪዎችን በአንድ መድረክ ለማገናኘት ተብሎ የተሰራ ቢሆንም ቻይናውያን ተጠቃሚዎች ከቻይና ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር መገናኘት አይችሉም።

በተጨማሪም ማንኛውም ፖለቲካዊ መልእክት ያለውን ገጽ ቻይናውያን እንዳያገኙት ይደረጋል።

ቻይና እሥር ቤት ያሉ ሙስሊም ዜጓቿን እያሰቃየች ነው

በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ የቻይና ዘመናዊ ባህሎች ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሬንሬን ያንግ እንደሚሉት የቻይና መንግስት ይህን ሁሉ ቁጥጥር የሚያደርገው ዜጎች ስለ ኮሙኒስት ፓርቲው እና ስለሃገራቸው ያላቸውን አመለካካት ለመቆጣጠር እንደሆነ ይናገራሉ።

የቻይና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ጉግል እና ዋትስአፕን መጠቀም ባይችሉም ባይዱ እና ዊቻት የተባሉ አማራጮች ቀርበውላቸዋል።