የኬንያ አስመጭዎች ውድ የባቡር መንገድ እንዲጠቀሙ መገደዳቸውን ገለፁ

በሞምባሳና በናይሮቢ መካከል የተዘረጋው የባቡር መስመር Image copyright MICHAEL KHATELI
አጭር የምስል መግለጫ በሞምባሳና በናይሮቢ መካከል የተዘረጋው የባቡር መስመር በቻይና ድጋፍ የተገነባ ነው

በኬንያ የሚገኙ አስመጭዎች ከወደብ ከተማዋ ሞምባሳ ወደ ዋና መዲናዋ ናይሮቢ እቃ ለማጓጓዝ ውድ የሆነውን እና አዲሱን የባቡር መስመር እንዲጠቀሙ በኬንያ የወደብ ባለሥልጣን መገደዳቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገለፁ።

ወደቡ ሕጉን ያፀደቀው ባሳለፍነው ነሐሴ ወር ቢሆንም ጥቅምት ወር ላይ በተፈጠረ ተቃውሞ ደንቡ እንዳይፈፀም መደረጉን ሮይተርስ ዘግቧል።

ወንበር የሚለቅላት አጥታ ልጇን ቆማ ያጠባችው እናት

ባቡር ላይ የተወለደችው ህጻን ለ25 ዓመታት ነጻ የባቡር ትኬት ተሰጣት

ለዜና ወኪሉ የገለፁት የንግድ ተቋማት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለውጥ ቢኖርም አሁንም ግን በጣም ውድ የሆነውን የክፍያ የባቡር መንገድ እንዲጠቀሙ መገደዳቸውን ይናገራሉ።

እነርሱ እንደሚሉት እቃዎቻቸውን ከተጨናነቀው የናይሮቢ የባቡር ጣቢያ ለመውሰድ የጭነት መኪናዎችን መላክ ስለሚጠበቅባቸው ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል። ይህም 50 በመቶ ለሚደርስ ተጨማሪ ክፍያ ይዳርጋቸዋል።

አስመጭዎች እቃዎቻቸውን ከናይሮቢ ወደብ ለማንሳት በትንሹ 25 ሺህ የኬንያ ሽልንግ ( 243 ዶላር ) ለእቃ ጫኝ መኪና መክፈል ግድ ይላቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ 15 ሺህ ሽልንግ ለእቃ ማራገፊያው ጣቢያ እንደሚከፍሉ ሦስት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነጋዴዎች ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

በመንግሥት የሚተዳደረው የኬንያ ወደብ ባለሥልጣን ኃላፊ እና የኬንያ የባቡር መስመር የቦርድ አባል የሆኑት ዳንኤል ማንዱኩ ከፍተኛ የሆነው ክፍያ የብድር ክፍያዎችን ለመፈፀም አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

እንደ ሮይተርስ ከሆነ በቻይና ኤግዚም ባንክ፣ በኬንያ የወደብ ባለሥልጣን እና በኬንያ የባቡር መስመር ያለው ስምምነት የኬንያ የወደብ ባለሥልጣን በዓመት አንድ ሚሊየን ቶን ካርጎ ለባቡር መስመሩ ማቅረብ እንዳለበት የሚጠይቅ ነው።

ኬንያ ለባቡር መስመሩ እና ለሌሎች ፕሮጀክቶች 660 ቢሊየን ሽልንግ የኤግዚም ባንክ ዕዳ አለባት። ይህ ማለት ደግሞ በአጠቃላይ አገሪቷ ካለባት እዳ 10 በመቶ ያህሉ ነው።

ባንኩና የኬንያ ወደብ ባለሥልጣን በጉዳዩ ላይ የሰጡት ምላሽ የለም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ