በመቀሌ 'ሕገ መንግሥትና ፌደራላዊ ሥርዓትን የማዳን መድረክ' እየተካሄደ ነው

ዶ/ር ደብረፅዮን በውይይት መድረኩ ላይ

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት "ሕገ መንግሥትና ሕብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ሥርዓትን ማዳን" በሚል መሪ ቃል ሁለተኛው አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ትናንት ሕዳር 23/2012 ዓ.ም ጀምሮ እያካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ክልልነት ለጠየቀው ሁሉ ቢሰጥ ችግሩ ምንድነው?

"የሽግግር መንግሥት ተግባራዊ መደረግ አለበት"

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው በአሁኑ ወቅት ያለው የሁሉንም ፍላጎት የማያስተናግድ፣ የጠቅላይነት አስተሳሰብ መኖር አገሪቷን ወደ ከፋ ሁከትና መበተን እንደሚያመራት ተናግረዋል።

"በአጠቃላይ በውስጥና በውጭ ኃይሎች በተተበተበ ሃገርን የማፍረስ እንቅስቃሴ ምክንያት፣ ለአደጋ ተጋላጭነታችንን እያየነው መጥተናል" ያሉት ዶ/ር ደብረፅዮን፤ ለሁሉም መሠረት የሆነው ሠላም መደፍረስ፣ የሕግ የበላይነት የማይከበርበት፣ የአገሪቷ ሕገ መንግሥት በግልፅ የሚጣስበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል።

ዜጎች በአገራቸው እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው መሥራት የተቸገሩበትና ለጥቃት የተጋለጡበት ወቅት ላይ መሆኑንም በማከል አገሪቷ በአደገኛና አስፈሪ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አስምረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያን ከዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ለማላቀቅ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? የቱን መንገድ መከተል ያሻል የሚሉትን ጥያቄዎች በመመለስ ከተጨማሪ ጉዳትና ጥፋት ማዳን እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

ሁሉም አገር ወዳድ አንድ ሃሳብ በመያዝ የተቀናጀ ሥራ መሥራት የግድ ይላል ብለዋል- ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ።

ዶ/ር ደብረ ፅዮን፤ መድረኩ ፓርቲዎችና ግለሰቦች የመሰላቸውን ሃሳብ በማንሸራሸር ትግል የሚያደርጉበት እንጂ፣ ሃሳብ ወደ መድረክ እንዳይመጡ የሚታፈኑበት ባለመሆኑ የፖለቲካዊ አጀንዳዎች በሰላምና፣ በሕጋዊ መንገድ በማካሄድ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱን የሚያጠናክር አጋዥ የፖለቲካ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

ዶ/ር ደብረፅዮን በንግግራቸው "የተለያየ ሃሳብ የሚፈሩ በውይይትና በመድረክ የማያምኑ ደካሞች፣ በዚህ መድረክ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች እንዳይሳተፉ በተለያየ መልኩ ጫና በማድረግ ፀረ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰባቸውን አሳይተዋል" ያሏቸውን እና ማንነታቸውን በስም ያልጠቀሱ አካላትን አውግዘዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ "የውጭ ጠላቶቻችን የአገራችንን መዳከም ብቻ ሳይሆን መበታተን የግድ አስፈላጊ ነው ብለው በግላጭ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው" በማለት ካለፈው ስህተት በመማር ቀጣይ የኢትዮጵያ ጉዞ የተቃና እንዲሆን ጠቃሚ ድምዳሜዎች ላይ የሚደረስበት መድረክ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል።

"ውስኪ ጠጪ ኢህአዴጎች እባካችሁ ውሃ የናፈቀው ሕዝብ እንዳለ አትርሱ" ጠ/ሚ ዐብይ

የብልጽግና ፓርቲ ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮምኛና ሌሎችም ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ወሰነ

ውይይቱ እየተከታተለ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢም የፌደራል ሥርዓት አደጋ ላይ እንደወደቀ፣ አገሪቷም ወደ ከፋ ደረጃ እየተሸጋገረች እንዳለች፤ የፌደራሊስት ኃይሎች፣ ሌሎች ብሔረሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች ተገናኝተው በመወያየት የፌደራል ሥርዓቱን የማዳን ዘመቻ ማካሄድ አለብን የሚል ፅኑ አቋም እንዳላቸው ተሳታፊዎች መግለፃቸውን ተመልክቷል።

ፌደራሊዝሙ አደጋ ላይ የመውደቁ ማሳያ ምንድን ነው?

'ፌደራሊዝም አደጋ ላይ ወድቋል' ተብሎ ለቀረበው ሃሳብ የተጠቀሰው አንዱ ምክንያት ኢህአዴግ ውስጥ የተካሄደው ውህደት መሆኑ በውይይቱ ላይ መነሳቱን ቢቢሲ ሰምቷል።

ምክንያቱንም ውህደቱ ወደ አሃዳዊ ሥርዓት የሚመራ ነው፤ ሌሎችን ጨፍልቆ የሚይዝና ከአሁን በፊት በትግል የተመሠረተውን ፌደራሊዝም የሚያጠፋ ነው ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው እንደኮነኑት በስፍራው የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ መረዳት ችሏል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረንስ ሊቀመንበር አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ፤ የውይይቱ አሰናጅ ሕውሓት አለመሆኑን በመጥቀስ ይጀምራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በተካሄደው የመጀመሪያው ውይይት ወቅት በተዋቀረው ኮሚቴ አማካኝነት 50 የሚሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንደተጋበዙ ይናገራሉ።

እርሳቸውም እዚህ ውይይት ላይ ሲካፈሉ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው።

"ባለፉት 27 ዓመታት የፌደራል ሥርዓቱ በዲሞክራሲ ተደግፎ አላደገም፣ ቋንቋን መግፋት፣ ማንነትን የመግፋት ሁኔታዎች ነበሩ" ሲሉ ያስታውሳሉ።

"ባለፉት 3 ዓመታትም ለውጥ መጥቶ ነበር" የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ ለውጡን ተቀብለው የመጡት የሕዝቡ ጥያቄ ትክክል መሆኑን ካመኑ በኋላ የሕዝቡን ጥያቄ ወደ መመለስና ሃገር ወደ ማረጋጋት ነው የሄዱት ብለዋል።

ይሁን እንጅ ሕገ መንግሥቱ ለዜጎች የሰጠው መብት እየተጣሰ ነው፣ ዜጎች እየተንቀሳቀሱ መሥራት አልቻሉም፣ በርካቶች ተፈናቅለዋል በመሆኑም ውይይቱ ሕገ መንግሥቱ ይከበር የሚል አንድምታ እንዳለው ያስረዳሉ።

የ31 ዓመቱ ኢሕአዴግ ማን ነው?

ህወሓት ከኢህአዴግ ለመፋታት ቆርጧል?

"አሁን ያለው አስተዳደርም የሕዝቡን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ 'መደመር' እሳቤ ነው ያመጡት" ይላሉ።

አቶ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲን ሕገ ወጥ ነው ይሉታል። ይሄ ፓርቲ ሕጋዊ ካልሆነ ማን ነው ሃገሪቱን እየመራ ያለው? ሕዝቡ በማያውቀው ፓርቲ እየተመራ ነው?" ሲሉም ይጠይቃሉ።

በመሆኑም እነዚህን ሃሳቦች ለመታገል እና ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝሙን እና ሕገ መንግሥቱን ለማክበር እየተካሄደ የሚገኝ ውይይት እንደሆነ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ትናንት የተጀመረው ይሄው ውይይት ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ