ኬንያዊቷ ታዳጊ አንድን ግለሰብ ከጎርፍ ለማዳን ስትጥር ህይወቷ አለፈ

የሞተችው ታዳጊ

አንዲት ኬንያዊት ታዳጊ አንድን ግለሰብ ከጎርፍ ለማዳን ስትጥር ሰምጣ ህይወቷ አልፏል።

ከመዲናዋ ናይሮቢ ወጣ ብሎ በሚገኘው ካንዲሲ የሚባል ወንዝ ገብታ ነው ህይወቷ ያለፈው፤ የአስራ ዘጠኝ ዓመቷ አን ዱኩ።

አን እየተገነባ በነበረ ድልድይ ስር አድኑኝ እያለ በመማፀን ላይ የነበረ ግለሰብን ጩኸት ሰምታ ነው ለእርዳታው የመጣችው። ግለሰቡ ህይወቱ ቢተርፍም እሷ ግን ወንዝ ውስጥ በመውደቋ ህይወቷ አልፏል።

"የቱሪስት ማግኔት" የሆነችው ቬኒስ ከተማን ጎርፍ እያስጨነቃት ነው

መሬት መንሸራተትና ጎርፍ በደቡብ ኢትዮጵያ ጥፋት አደረሰ

እናቷ ኤልዛቤት ሙቱኩ ለቢቢሲ ጋዜጠኛ እንደተናገሩት "ወንዝ ውስጥ ስትታገል አየሁዋት፤ ህይወቷንም ለማዳን ሞክሬያለሁ። 'አና አና' ብዬ እየጠራሁዋት ነበር። እሷንም ለመጎተት እንዲያስችለኝ እንጨት መወርወር አስቤ ነበር። ነገር ግን የወንዙ ማዕበል በጣም ከፍተኛ ስለነበር፤ ልጄን ጥርግ አድርጎ ወሰዳት" በማለት እንባ እየተናነቃቸው ተናግረዋል።

በዚህ ሳምንት ከሰኞ ጀምሮ በምሥራቅ አፍሪካ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጥል የነበረውን ዝናብ ተከትሎ ነው ወንዙ ከመጠን በላይ የሞላው።

ነገር ግን ነዋሪዎች እንደሚሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰባት ሰዎች በወንዙ ተወስደው ለሞት ተዳርገዋል።

ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቅ ለምን አስፈለጋት?

በቴክኖሎጂ ኢ-ፍትሐዊነትን የምትታገለው ኢትዮጵያዊት

ወንዙን ለመሻገር ያገለግል የነበረው አሮጌ ድልድይ ከሁለት ዓመት በፊት የፈረሰ ሲሆን አዲሱ ድልድይ ባለመጠናቀቁ ነዋሪዎች ድንጋይ ከላይ በመደርድር እየተሻገሩ መሆኑ ተገልጿል።

የሟቿ ታላቅ እህት ማርያም ዜኔት ለቢቢሲ እንደገለፀችው መንደራቸውን ከዋናው ገበያ ጋር የሚያገናኘው ድልድይን ማጠናቀቅ የአካባቢው ባለስልጣናት ኃላፊነት ቢሆንም፤ ይህንን ባለማድረጋቸውም ጥፋተኞች ናቸው ብላለች።

"ባለፉት ሁለት ዓመታት ብዙ ሰዎች ድልድዩን ሊያቋርጡ በሚሞክሩበት ወቅት ህይወታቸው አልፏል። ባለስልጣናቱ መጥተው ሃዘናቸውን ከመግለፅ ውጪ ምንም ያደረጉልን ነገር የለም። ዛሬ እህቴ ሞተች? ነገስ ቀጣዩ ማነው? ድልድዩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱም የሚመላለሱበት ነው። አዲስ መገንባት ካልቻሉ የድሮውን ለምን አፈረሱት?" በማለትም ትጠይቃለች።

በልጃቸው ሞት ልባቸው የተሰበረው እናት "በጣም አዝኛለሁ። የወደፊቱ መሪ፤ ወይም መምህር ትሆን ነበር። በዚህ ድልድይ ምክንያት የልጄን ሕይወት ማጣቴ ህመሜን አክብዶታል" ብለዋል።