ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን ጂቡቲ ውስጥ ለማቋቋም የተደረሰ ስምምነት የለም ተባለ

የጂቡቲ ወደብ Image copyright Getty Images

እስካሁን ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን በጂቡቲ ለማቋቋም የተደረሰ ስምምነት እንደሌለ ተገለጸ።

የባሕር በር አልባዋ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን ሦስት አስርት ዓመታት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ጂቡቲ ውስጥ መልሳ ልታቋቁም መሆኗ ተነግሯል።

ባለፈው ሳምንት ካፒታል የተባለው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታተም የእንግሊዝኛ ጋዜጣ የኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን ጂቡቲ ውስጥ እንደምታቋቁምና ዋና የማዘዣ ጽህፈት ቤቱም በባሕር ዳር ከተማ እንደሚሆን ዘግቦ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን መልሳ የማደራጀት ፍላጎት እንዳለት በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በይፋ መነገሩ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የጂቡቲ አምባሳደር የሆኑት መሐመድ እድሪስ ፋራህ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጉዳዩን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና የጂቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኢል ኦማር ጊሌ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ እንዳሉት የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል ጂቡቲ ውስጥ ማቋቋምን በሚመለከት ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸውን ያመላከቱ ሲሆን፤ ነገር ግን "እስከ አሁን የተደረሰ ህጋዊ ስምምነት የለም" ብለዋል።

አምባሳደሩ አክለውም በሁለቱ አገራት መካከል የባሕር ኃይልን ማቋቋምን በተመለከተ በሚደረገው ማንኛውም ስምምነት ላይ ኢትዮጵያና ጂቡቲ ብቻ ሳይሆኑ "የባሕር ኃይሉን በማቋቋሙ ሂደት ድጋፍ የምታደርገው ፈረንሳይም" እንደምትኖር ጠቅሰዋል።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተለየችበት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ፤ የባሕር ኃይል ሳይኖራት ቆይታ ከቅርብ ዓመታት በኋላ መልሳ የማቋቋም ፍላጎት እንዳላት በተለያዩ አጋጣሚዎች ብትገልጽም ይህ የባሕር ኃይል መቀመጫውን የት እንደሚያደርግና በምን ሁኔታ እንደሚቋቋም በኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ ዝርዝወር መረጃ የለም።

ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ኢትዮጵያ በፈረንሳይ ድጋፍ ለማቋቋም ያቀደችው የባሕር ኃይል መቀመጫውን በኤርትራዋ የምጽዋ ወደብ እንደሚሆን 'ዠን አፍሪክ' ለተሰኘው የፈረንሳይ መጽሔት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ገልጸው ነበር።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በኢትዮጵያ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ወቅት ኢትዮጵያ ለማቋቋም የምትፈልገውን የባሕር ኃይል ሠራዊት እውን ለማድረግ አገራቸው አስፈላጊን ድጋፍ እንደምታደርግ ተናረው ነበር።

ኤርትራ ነጻነቷን እስካገኘችበት እስከ ግንቦት ወር 1983 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያ በምጽዋና በአሰብ ወደቦች ላይ ትልቅ የባሕር ኃይል ነበራት።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ እና ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር እና ሃገር መከላከያ የህዝብ ግነኙነት ቢሮዎች እንዲሁም ወደ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስልክ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ