ጀርመን ሁለት የሩሲያ አምባሳደሮችን አባረረች

Crime scene in Moabit, Berlin, 23 Aug 19 Image copyright AFP

ከወራት በፊት በበርሊን የሕዝብ ፓርክ ውስጥ ለተፈጸመው ግድያ ትዕዛዙ የተሰጠው በሩሲያ ወይም በቺቺኒያ ሪፐብሊክ ሳይሆን አይቀርም በማለት ጀርመን መቀመጫቸውን በርሊን አድርገው የነበሩ ሁለት የሩሲያ አምባሳደሮችን አባረረች።

ይህ የጀርመን መንግሥት ውሳኔ የተሰማው የወንጀል ምርመራውን የሃገሪቱ ዋና አቃቤ ሕግ ከያዘው በኋላ መሆኑ ታውቋል።

ሩሲያ በበኩሏ አምባሳደሮቹ እንዲባረሩ መደረጉን እና ግድያው የተፈጸመው በሩሲያ መንግሥት ትዕዛዝ ሳይሆን አይቀርም መባሉን አጥብቃ ኮንናለች።

ሩሲያ "መሠረተ ቢስ" በማለት የጀርመንን ውሳኔ ያጣጣለች ሲሆን፤ አጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ጭምር ዝታለች።

ጀርመን ሩሲያ በወንጀል ምርመራው ላይ ትብብር እያደረገች አይደለም ስትል ትከሳለች።

ከአራት ወራት በፊት የቀድሞ የቺቺኒያ አማጺያን ኮማንደር የነበረው የ40 ዓመቱ ጎልማሳ ዜሊምካሃን ክሃንጎሽቪሊ በርሊን ከተማ በሚገኝ ፓርክ ውስጥ እንዳለ ነበር ከጀርባ በኩል ጭንቅላቱን በጥይት ተመቶ የተገደለው።

ግለሰቡን ሳይገድል አይቀርም የተባለው ተጠርጣሪ ከቀናት በኋላ በጀርመን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ቢውልም፤ ከተጠርጣሪው የተገኘው መረጃ ግን አጥጋቢ አለመሆኑ ተነግሯል።

አቃቢ ሕግ ተጠርጣሪው ግድያው ከመፈጸሙ ስድስት ቀናት በፊት ከሞስኮ ተነስቶ ወደ አውሮፓ እንደመጣ ተናግረዋል።

ግድያው ከተፈጸመ በኋላ የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ሃገራቸው ከግድያው ጋር ምንም የሚያገናኛት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ሟቹ ዜሊምካሃን ክሃንጎሽቪሊ ማን ነበር?

Image copyright facebook
አጭር የምስል መግለጫ ዜሊምካሃን ክሃንጎሽቪሊ (ቀኝ) በሩሲያ ልዩ ኃይል የተገደሉት የቀድሞ የቺቺኒያ ፕሬዝደንት አስላን ማስካሃዶቭ (ግራ) የልብ የቅርብ አጋር ነበር።

የጆርጂያ ዜግነት ያለው የ40 ዓመቱ ዜሊምካሃን ክሃንጎሽቪሊ፤ የቺቺኒያ አማጺያን ኮማንደር ሆኖ የሩሲያ ጦርን እአአ ከ2001-2005 ድረስ ተዋግቷል።

ዜሊምካሃን በሩሲያ ልዩ ኃይል የተገደሉት የቀድሞ የቺቺኒያ ፕሬዝደንት አስላን ማስካሃዶቭ የቅርብ አጋር ነበር።

የቀድሞ የአማጺያን ኮማንደሩ ዜሊምካሃን እአአ 2015 ላይ በትውልድ ሃገሩ ጆርጂያ መዲና ትብሊስ የግድያ ሙከራ ከተደረገበት በኋላ ነበር ወደ ጀርመን በማቅናት ጥገኝነት የጠየቀው፤ ምንም እንኳ የጥገኝነት ጥያቄው ከጀርመን መንግሥት ይሁንታ ባያገኝም።

ቺቺኒያ በአሁኑ ወቅት ለሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ታማኝ በሆኑት ራመዛን ካድይሮቭ ትመራለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ