"ምንም ነገር ሰርቄ አላውቅም" የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ

ፕሬዚዳንት ዩዌሬ ሙሴቬኒ ሰልፉን ሲመሩ Image copyright Getty Images

በኡጋንዳ ዛሬ በተካሄደውና ሙስናን ለመዋጋት ባለመው ሰልፍ ላይ ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ "ከማንም ምንም ነገር አልሰረቅኩም እናም ድሃ አይደለሁም" ሲሉ መደመጣቸውን ኒው ቪዥን ጋዜጣ ዘገበ።

ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት በሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በተሳተፉበት እና እርሳቸው በመሩበት ሰልፍ ወቅት ነው።

"ሙሰኛ ሰዎች ጥገኛ ተህዋስ ናቸው፤ ምክንያቱም ያለፉበትን ሐብት ያካብታሉ" ሲሉም ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው አክለዋል።

ጋዜጣው እንደዘገበው የፕሬዚደንቱ ንግግር የተደመጠው የሃገሪቱ የህዝብ እንደራሴ ምክትል ቃል አቀባዩ ጃኮብ ኦውላንያህ " ክቡር ፕሬዚደንት ማን ነው ሙሰኛ? ሙሰኞቹ ሚስቶች፣ ባሎች፣ እህት፣ ወንድም፣ አባት ወይ እናቶቻችን ናቸው። ሙሰኞች አያቶቻችን ናቸው። ሙሰኞች የምንኖርበት ማህበረሰብ ነው፤ ክቡር ፕሬዚደንት ሁላችንም ሙሰኞች ነን!" ሲሉ ከተናገሩ በኋላ ነበር።

ይሄው ሙስናን ለመዋጋት የተደረገው ሰልፍ በዋና መዲናዋ የትራፊክ መጨናነቅ የፈጠረ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች መንግሥት ያዘጋጀውን ይህን ዘመቻ በተመለከተ በትዊተር ገፃቸው ላይ "ሙስና ራሱ ዘመቻውን ለመቀላቀል መንገድ ላይ ነው" የሚሉና ሌሎች ሃሳቦችን በማስፈር ወርፈዋል።

ተያያዥ ርዕሶች