"ማርታ፣ ለምን ለምን ሞተች?"

ማርታ መብራህቱ Image copyright ማርታ መብራህቱ

ያች እለት! ከአርባ ሰባት አመታት በፊት 94 መንገደኞችን የያዘች ቦይንግ 720 በአስመራ በኩል ወደ ፓሪስ ለማቅናት ከአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት ተነሳች።

የበረራ ቁጥር 708፣ ንብረትነቷም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነበረች።

እንደተለመደው ተጓዥ በሙሉ በየእምነቱ ጸሎት አድርሶ፣ አገር ሰላም ብሎ የፍቅር ከተማ ብለው ወደሚጠሯት ፓሪስ ለመድረስ ተስፋ ሰንቋል።

ከመንገደኞቹ መካከልም ማርታ መብራህቱ፣ ዋልልኝ መኮነን፣ አማኑኤል ዮሃንስ፣ ጌታቸው ሃብቴ፣ ታደለች ኪዳነማርያም፣ ዮሃንስ ፍቃዱ እንዲሁም ተስፋየ ቢረጋ ነበሩበት።

"ማንም መብታችንን ሊሰጠን ስለማይችል፤ ሴቶች ማንንም ሳይጠብቁ በራሳቸው መታገል አለባቸው"

የተነጠቀ ልጅነት

የተማሪዎች እንቅስቃሴን ታሪክ ለሚያውቅ እነዚህ ወጣቶች ምን ያህል የእንቅስቃሴው ቁንጮ እንደሆኑ መረዳት ቀላል ነው።

ስር ነቀል ለውጥን በማቀንቀንና መሬትን ለአራሹ በሚል እንቅስቃሴያቸው የአብዮቱ ጠባቂ (ዘ ጋርዲያን ኦፍ ዘ ሪቮሉሽን) ተብሎ በሚጠራው በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የነማርታ መብራህቱ ስም የገነነ ነበር።

በ1953 ዓ.ም የተካሄደውና በጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ የተጠነሰሰው መፈንቅለ መንግሥት ምንም እንኳን ባይሳካም ለውጥን ያበሰረ እንዲሁም ስርዓቱን መገርሰስ እንደሚቻል ያመላከተ ነበር።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በተለያዩ ሃገራት ያሉ እንቅስቃሴዎች የተጋጋሉበት ወቅት ነበር። በወቅቱ ይፃፉ ነበሩ የትግል ጥሪዎችን ለምሳሌ ብንወስድ፤ የአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ልሳን ከነበረው ታጠቅ የሚከተለው ፅሁፍ ሰፍሮ ነበር።

"በፊውዳሊዝም እና በኢምፔሪያሊዝም መቃብር ላይ የሁላችን የሆነች ህዝባዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት ኢትዮጵያውያን የሆንን ሁሉ እፍኝ ከማይሞሉት ጨቋኝና ደጋፊዎቻቸው በቀር በአንድ የትግል ግንባር ውስጥ ተሰብስበንና ተደራጅተን በአንድነት መራመድ አለብን"

ምንም እንኳን መሳፍንቱም በአልበገር ባይነት ሙጭጭ ቢሉም የተንሰራፋው ስራ አጥነት፣ ረሃብ እንዲሁም ኢፍትሃዊነት መስፈን ትግሉን አቀጣጠለው።

ትግሉ ተጋጋለ፣ "መሬት፣ መሬት፣ መሬት ላራሹ፣ ተዋጉለት አትሽሹ" የሚሉ መፈክሮች፣ ሰላማዊ ሰልፎችና የስራ አድማዎች መጠናከር ስርዓቱን ያንገዳግዱት ጀመር።

ተቃውሞን ለመገለጽ ተግባር ላይ ይውሉ ከነበሩት የትግል መንገዶች መካከል አንዱ የአውሮፕላን ጠለፋን ማካሄድ ዋነኛው ነበር።

ለአውሮፕላን ጠለፋ ተልዕኮም ነበር እነ ማርታ መብራህቱ በበረራ ቁጥር 708 የተሳፈሩት፤

ማርታ ከትግል ጓዶችዋ ጋር አውሮፕላን ለመጥለፍ ከመጓዟ ቀደም ብላ በዘውዳዊው ስርዓት ላይ የነበራትን ጠንካራ አቋምና የነገ ህልሟ የሚገልጽ ጽሑፍ "ማኒፌስቶ" ትታ ነበር የተሳፈረችው። ይሄው መልእክት እንዲህ ይነበባል።

"የመከላከያ ሚኒስቴርን በተሻለ መልኩ መምራት ይቻላል" ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

"እኛ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሴቶች ትግላችንን ለመጀመር ዝግጁ መሆናችንን ለማሳየት ለዓለም ህዝብ የምናሳውቅበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ትግላችን ትልቅ መስዋእትነት የሚጠይቅና ጉልተኞችና አጼዎችን የሚመክት ይሆናል። በዚሁ የትግል ማዕበል ጭቁን ህዝባችንን ለማዳን ቆራጦችና የማንወላወል መሆን አለብን። ጠላቶቻችን እንዲህ ዓይነት ቋንቋ ብቻ ነው የሚገባቸው። ነጻነትም ይሁን እኩልነት መና ሆኖ ከሰማይ አይወርድም። በተለይ እኛ ሴቶች ደግሞ የበለጠ የተጨቆንን ስለሆን፤ በርትተን፤ ታጥቀን መታገል አለብን። ጥረታችንም ሆነ ለውጥ ፈላጊነታችን ከሁሉም በላይ ሊሆን ይገባል።"

ማርታ መብራህቱ ን ናት?

ማርታ ውልደቷ በ1943 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን፤ ትምህርቷን በደብረ ዘይት እንዲሁም አባቷ በስራ ምክንያት ወደ ናይጀሪያ ሲሄዱ በዛው አጠናቃለች። በወቅቱም አሜሪካን የመጎብኘት እድል ያገኘችው ማርታ ዓለም አቀፉን የጭቆና ትግሎችን በተለይም በአሜሪካ ውስጥ የሚደረገውን የሲቪል መብቶች ትግል መረዳት አስችሏታል።

የኢትዮጵያ ትግል ለብቻው እንዳልሆነና በተለይም ከዓለም አቀፉ ፀረ- ኢምፔሪያሊዝም፣ ቅኝ ግዛት እንዲሁም ዘረኝነት ትግሎችም ጋር አብሮ እንደሚቆም በማኒፌስቶዋ ገልፃለች። አሜሪካ በቬትናም ላይ ያደረገችውን ወረራ በመቃወም፣ የፍልስጥኤምን ጥያቄ እንዲሁም በላቲን አሜሪካ ለነፃነት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ ቆማለች።

"ድል ለታጋዩ ህዝብ፤ ወንድሞቼና እህቶቼ በትግላችን እንቀጥል" በማለትም ለትግሉ ያላትን ፅኑ አቋም አንፀባርቃለች። ምንም እንኳን በወቅቱ አባቷ ምህንድስና እንድትማር ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም እሷ ግን በዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቀድሞው ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ገና በአስራ አምስት አመቷ ህዝቡን ለመርዳት ካላት ፍላጎት ጋር ተያይዞ የህክምና ትምህርቷን ለመከታተል ተቀላቀለች።

በወቅቱም የአርሶ አደሩ ሁኔታ፣ የሰፈነው ድህነትን ትታገል ነበር ፤ ትግሉ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ብዙ የታገለች ሲሆን ጓደኞቿም በጥቁር አሜሪካ የትግል ታሪክ ዘንድ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጣት አንጄላ ዴቪስ ጋር ያመሳስሏት ነበር ማርታ "ኢትዮጵያዊቷ አንጄላ ዴቪስ"።

ማርታ አይበገሬ፣ አንደበተ ርቱዕ፣ አንባቢ፣ የህዝብ በደል የሚያንገበብግባት ነበረች፤ በተማሪዎች እንቅስቃሴም የጎላ አስተዋፅኦ ነበራት። በትምህርቷ በጣም ጎበዝ የነበረች ሲሆን የህክምና ተማሪዎች ማህበርም ፕሬዚዳንት ነበረች።

አባቷ ራሳቸው እንዴት እንዲህ አይነት ጨቋኝ ስርአት አካል ትሆናለህ በማለትም በከፍተኛ ሁኔታ ትተቻቸው እንደነበር ተናግረዋል። በአንድ ወቅትም መሬት መግዛታቸውን ስትሰማ "እኛ መሬቱን ለአራሹ ለባለቤቱ ለማስመለስ እንጥራለን፤ አንተ መሬት ትገዛለህ" ማለቷን ነብዩ ሃይለሚካኤል 'Life in Twentieth century Ethiopia Autobiographical Narrative of Brigadier General Mebrahtu Assefa' በሚለው የመመረቂያ ፅሁፉ አካቶታል።

ማርታ ትምህርቷን ጨርሻ ዶከተር ለመሆን አንድ ሴሚስተር ሲቀራት ነበር ከትግል ጓደኞችዋ ጋር በጠለፏት አውሮፕላን ሰማይ ላይ የቀረችው።

የእርሷና የትግል ጓዶቿ የአውሮፕላን ጠለፋ ወሬ በሰላዮች ጆሮ መግባቱ ጋር ተያይዞ መጨረሻቸውን የሚያሳዝን አድርጎታል።

የአውሮፕላኑ ጠለፋ

ሕዳር 29፣ 1965 ዓ.ም ከዋለልኝ መኮንን፣ ከአማኑኤል ዮሃንስ፣ ከጌታቸው ሐብቴ፣ ከዮሃንስ በፍቃዱ፣ ከተስፋዬ ቢርጋናና ከታደለች ኪዳነ ማርያም ጋር አውሮፕላኑን ለመጥለፍ አልመው ገቡ። ዋለልኝ ሰባራ ሽጉጥ ይዟል፣ ማርታ በበኩሏ የእጅ ቦምብ ይዛ እንድትገባ በተሰጣት ትዕዛዝ መሰረት በውስጥ ሱሪዋ (በፓንትዋ ይዛው ገባች)።

ጥበቃውን አልፈው ቦታውን ያዙ፤ አውሮፕላኑም በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት ሊበር ማንኮብኮብ ጀምሯል። አውሮፕላኑ ከተነሳ ከአስራ ሶስት ደቂቃ በኋላ አንድ ሽጉጥ የያዘና ቦምብ የያዘ ግለሰብ " አውሮፕላኑ ተጠልፏል፤ አርፋችሁ ተቀመጡ" አለ።

የፀጥታ ኃይሉ ተኮሰበት፤ የያዘውን የእጅ ቦምብም ማፈንዳት አልቻለም። ማርታ እሱን ለመከለል በትግል ጓደኛዋ ላይ ወደቀች፤ አልተረፈችም! ተተኮሰባት።

ከጠላፊዎቹ መካከል አማኑኤል ዮሃንስ ቦምብ ይዞ ነበር፤ አማኑኤል በአውሮፕላን ጠለፋ ላይ ሲሳተፍ ለሁለተኛ ግዜው ነው።አውሮፕላኑ በጠላፊዎች እጅ ስለገባ ባለበት እንዲቆይ ቀጭን ትዕዛዝ ተላለፈ፤ ሰማይና ምድር የተገለባበጡ ይመስል ሁኔታዎች ተቀያሩ። በነዛ ወጣቶች ላይ የተኩስ እሩምታ ተከፈተባቸው፤

በተዓምር ከተረፈችው ከታደለች ኪዳነ ማርያም በስተቀር ፤ ሰባቱም ተገደሉ። አውሮፕላኗ በደም አበላ ተሞላች።

ገና በ22 አመቷ የተቀጨችው ማርታ፤ ባለ ትልቅ ስሟ ማርታ መሞቷ የእግር እሳት የሆነባቸው አባቷ " ይህንን ስርአት አገልግያለሁ እና ጨክኖ ይገድላታል ብዬ አላሰብኩም ነበር" ማለታቸውን ነብዩ ሃይለሚካኤል በፅሁፉ አካቶታል።

የነሱ ሞት ትግሉን አቀጣጠለው፤ ወላጆች አነቡ፤ እናቶች ልባቸው ተሰበረ፤ ተማሪዎች ዘመሩላቸው " ጥላሁን፣ ለምን ለምን ሞተ?፣ ማርታ ለምን ለምን ሞተች? ገርማሜ ለምን ለምን ሞተ? ታከለ ለምን ለምን ሞተ? በኃይል በትግል ነው፤ ነፃነት የሚገኘው"

"ማርታ ለሀገርሽ ራስሽን ሰጥተሻል፤ ስምሽ የማይሞት ነው ዘላለም ይኖራል፤ ለቀሩት እህቶሽ ምሳሌ ሆነሻል ተባለላት፤

የሴቶች መብት ታጋይዋ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ማን ናቸው?

የአውሮፕላን ጠለፋ እንደ ትግል ዘዴ

በስልሳዎቹ የአውሮፕላኖች ጠለፋ ለዘውዳዊት መንግሥት ትልቅ ስጋት ፈጥሮበት እንደነበር የታሪክ ተንታኞች ይናገራሉ። በተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ (ተሓኤ) የተመለመሉ ወጣቶች በውጭ አገር በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን አየር መንገድ አውሮፕላኖች ይጠልፉ የነበረ ሲሆን፤ ቀስ በቀስም ከኢትዮጵያውያን ጓዶቻቸው አብረው የጠለፋውን ስራ ተያያዙት።

በጎርጎሳውያኑ 1969 ዓሊ ስዒድ ዓብደላ የተባለ የህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ ታጋይ ከሁለት ጓዶቹ ተባብሮ በካራቺ ፓኪስታን የኢትዮጵያን አየር መንገድ በመጥለፍ ከባድ ጉዳት አደረሱ።

ዓሊ ስዒድ በስልሳዎቹ ወደ ትጥቅ ትግል የተሰማራና ከመስራቾቹ አንዱ ነው። በትጥቁ ትግል ጊዜም የአብዮት ዘብ የሚባለውን የድርጅቱ ክፍል በሃላፊነት መርቷል።

የታሪክ ተማራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በኢንሳይክሎፒድያ ኢትዮፒካ ስለ ብርሃነ መስቀል ረዳ እንደሚከተለው ጽፈዋል።

በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 1969 ብርሃነ መስቀል ከእነ አማኑኤል ገብረየሱስ፣ እያሱ አለማየሁ፣ ገዛኸኝ እንዳለና ሌሎች ጓዶቹ አብሮ አውሮፕላን ጠልፈው በአልጀርያ ጥገኝነት እንደጠየቀና በመቀጠልም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) መመስረቱን ፅፈዋል።

ባህሩ ዘውዴ " The Quest for Socialist Utopia" በሚለው መጽፋሃቸውም በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ1971 በወቅቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የነበሩት ሙሴ ተስፋሚካኤል፣ ዮሃንስ ስብሃቱ፣አማኑኤል ዮሃንስ፣ ደበሳይ ገብረስላሴ ከባህርዳር ወደ ጎንደር ትበር የነበረች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ጠልፈው ወደ ሊብያ እንደሄዱም ፅፈዋል።

አውሮፕላኑን ከጠለፉት መካከል ሁለቱ ሙሴና ዮሃንስ በጎርጎሳውያኑ 1973 በህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ ድርጅት በዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ጥያቄ በማንሳታቸው አክራሪ ግራዘመም ናችሁ ተብለው እንደተገደሉ ኤርትራዊው ፕሮፌሰር ጋይም አስፍሯል።

አማኑኤል ዮሃንስ ደግሞ በድጋሚ አውሮፕላን ሊጠልፍ ሲል በጸጥታ ኃይሎች ተመትቶ ህይወቱ አልፏል።

የማርታ ቤተሰብ ቅድመ ታሪክ

ማርታ የብርጋዴር ጄነራል መብራህቱ ፍስሃና ወ/ሮ አርያም ገብረየሱስ የበኸር ልጅ ስትሆን፤ አራት ወንድምና እህቶችም አሏት።

አባቷ ጄነራል መብራህቱ የተወለዱት አስመራ ሲሆን አያቷም አቶ ፍስሃ አስመራ ውስጥ ገዛ ከኒሻ እየተባለ የሚጠራ ሰፈር ነበር ተወልደው ያደጉት።

አያቷ አቶ ፍስሃ በጎርጎሳውያኑ 1923ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ተከትሎ አባቷ ጄነራል መብራህቱ ያደጉት አዲስ አበባ እንዲሁም አሰበ ተፈሪ ነው።

ትምህርታቸውንም በአዲስ አበባ ዳግማዊ ሚኒልክ ነው ያጠናቀቁት።

በጣልያን ወረራ ጊዜ አያቷ በራስ እምሩ ሃይለስላሴ ስር ሆነው ጣልያንን ተዋግተዋል። የሞቱትም ገራ በተባለ ቦታ ላይ በተካሄደው ውጊያ ነው።

በዚህም ምክንያት የጄነራል መብራህቱ ቤተሰብ ወደ አስመራ ተመልሰው ለመኖር የተገደዱ ሲሆን በአስመራ ከሚስዮናውያን ጋር ትምህርታቸውን ቀጥለዋል።

በጎርጎሳውያኑ 1936 ዓ.ም እንግሊዝ ኤርትራን ለመቆጣጠር በከረን በኩል ሲገባ አባቷ ጄነራል መብራህቱ መንገድ ላይ ቆመው ነበር የተቀበሉዋቸው። ከእንግሊዞች ጋር ሆነው ለመስራት ፍቃደኛ እንደሆኑና የአባታቸውም ሞት ያንገበግባቸው ስለነበር ለመበቀል እንደሚፈልጉም ገለጹላቸው።

እንግሊዞችም ተርጓሚ ያስፈልጋቸው ስለነበር ጄነራል መብራህቱን ተርጓሚ አድርገው ቀጠሩዋቸው።

በወቅቱ ገና የ17 ዓመት ልጅ ነበሩ፤ የጣልያንኛና እንግሊዝኛ ቋንቋ ጥሩ ችሎታ ነበራቸው። ማርታ ከእንደዚህ ዓይነት ቤተሰብ ነበር የተወለደችው።

በትንሽ እድሜ ትልቅ ስራ የሰራች፤ ትውልድን ያነቃቃችው ማርታ መካነ መቃብር 'ጴጥሮስ ወጳውሎስ' ሲሆን መቃብሯም ላይ "እጆቼ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አንስቼ፤ ወደ አንተ ስለምን፤ ጸሎቴን ስማው" መዘዝ8፡3] የሚል የመጽሃፍ ቅዱስ ጥቅስ አርፎበት ይገኛል።