''በፍርሀት የምንኖርና በሃገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ የምንቆጠር ሰዎች ሆነናል''

Spike in anxiety levels

የፎቶው ባለመብት, Nikita Deshpande/BBC

ልክ እንደ አብዛኛዎቹ ህንዳውያን ሙስሊሞች የወደፊቱ እጣ ፈንታዬ ምን ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ነው ቀናቶቼን የማሳልፈው።

በሀይማኖቴ ምክንያት ስራ አላገኝ ይሆን? ተከራይቼ ከምኖርበት ቤት እባረር ይሆን? የደቦ ጥቃት ይደርስብኝ ይሆን? ይሄ ፍራቻዬ ማብቂያ ይኖረው ይሆን?

በዩኒቨርሲቲያችን አለመረጋጋት ተከስቶ በነበረበት ወቅት እናቴ '' አይዞሽ ትዕግስት ይኑርሽ'' ብላኝ ነበር ትላለች በህንዷ ዋና ከተማ ኒው ደልሂ በሚገኘው ጃሚያ ሚሊያ ኢዝላሚያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን የምትከታተለው ሪካት ሀሽሚ።

በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተደብድበዋል፣ በቤተ መጻህፍትና የተማሪዎች ማደሪያ ውስጥ ጭምር አስለቃሽ ጭስ ጥቅም ላይ ውሏል፤ ይሄ ሁሉ የሆነው ሀገሪቱ ያወጣችውን አዲስ ህግ ለመቃወም የወጡትን ተማሪዎች ለማስቆም ነበር።

በአዲሱ ህግ መሰረት ጥቃት የሚደርስባቸውና ከሌሎች ሀገራት የሚመጡ የስድስት ሀይማኖት ተከታዮች የህንድ ዜግነት የሚያገኙ ሲሆን ከባንግላዲሽ፣ ፓኪስታን እና አፍጋኒስታን የሚመጡ ሙስሊሞች ግን ዜግነት ማግኘት አይችሉም።

ሙስሊሞች ተመርጠው እንዲገለሉ የተደረገ ሲሆን ይህ ህጋዊ የማግለል ሂደት ነው ለበርካታ ተማሪዎች ለተቃውሞ ወደ መንገድ መውጣት ምክንያት የሆነው።

''ፖሊስ ተማሪዎቹ መኪናዎችን በእሳት እንዳቃጠሉና አመጽ እንዲነሳ ማድረጋቸውን ገልጿል፤ ነገር ግን የሚያቀርቡት ምንም አይነት ማስረጃ የላቸውም'' ትላለች።

''ማንም ሰው ጉዳት አልደረሰበትም ይላሉ፤ ታዲያ ተጎድተው ሆስፒታል የተኙት ተማሪዎች ከየት መጡ? ''

በኒው ደልሂ ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ህክምና በማጥናት ላይ ሲሆን የምገኘው እስከዛሬ በነበረኝ ቆይታ በርካታ ሰላማዊ የሆኑ ተቃውሞዎችን ተመልክቻለው።

የተቃውሞዎቹ አካል ባልሆንም ነገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቁጥጥር ውጪ ሲሆኑ ተመልክቻለሁ፤ በግርግሩም ተጎጂ ሆኛለሁ። ፖሊስ ተማሪዎች ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን ሲፈጽም ተመልክቻለሁ።

ፖሊሶች ወደ ማደሪያ ክፍሎቻችን ሲመጡ አስታውሳለሁ። የክፍሉን መብራት አጥፍተን የሌለን ለማስመሰል ሞክረናል። እንደ እድል ሆኖ ፖሊሶቹ ሳያገኙን ምሽቱ አለፈ።

ነገር ግን ትንሽ ቆይተን አንድ ነገር ተገነዘብን። ፖሊሶቹ ግቢውን ሲያስሱ የነበረው መንግሥትን ለመቃወም የወጡትን ብቻ ፍለጋ ሳይሆን ሙስሊሞችን እንደሆነ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በልጅነቴ በርካታ የሂንዱ ሃይማኖት መዝሙሮችን እየሰማሁ ከእንቅልፌ ስነቃ አስታውሳለሁ።

ሙስሊም ቤተሰቦቼ በብዛት የሂንዱ ሀይማኖት ተከታዮች በሚኖሩበት ምስራቃዊ ኦዲሻ ግዛት ነበር ጎጇቸውን የቀለሱት። ሁሌም ቢሆን በዓላት ሲደርሱ ተሰባስበን ነበር የምናከብረው።

የኢድ በአል ላይ ሂንዱ ጎረቤቶቻችን እኔና ወንድምና እህቶቼን እጃችን ላይ ሂና ሲቀቡን አስታውሳለሁ።

አንዳንድ የሂንዱ ሀይማኖት ተከታይ ጓደኞቼ ደግሞ በሩዝና በስጋ በቆንጆ ሁኔታ የሚሰራውን 'ቢርያኒ' ለመብላት ወደቤታችን ይመጡ ነበር።

ከምንኖርበት አካባቢ መስጂድ ባይኖርም አባቴ ግድ አልነበረውም፤ ምክንያቱም እስልምናን አይከተልም ነበር። እናቴ ግን በቤት ውስጥ በቀን አምስት ጊዜ የሰላት ጸሎት ታደርስ ነበር።

በጣም ብዙ የሂንዱ ሃይማኖት ተከታዮች በሚማሩበት ትምህርት ቤት ነበር የምማረው፤ አንድም ቀን ስለሀይማኖታችን ልዩነት ስናወራ አላስታውስም።

እስከ አሁኗ ሰአት ድረስ ሙስሊምነቴ መለያዬ ሆኖ አያውቅም ነበር። አሁን ነገሮች ሁሉ በፍጥነት ተቀያይረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ 'ስጋ ተመጋቢዎቹ' እየተባልን መለየት ተጀምሯል። ማህበረሰቡን የሚበክሉ ደፋሪዎች፣ ፓኪስታንን የሚደግፉ አሸባሪዎችና ህንድን ለመቆጣጠር የተነሱ ማህበረሰቦች ናቸው እንባላለን።

እውነታው ግን በፍርሀት የምንኖርና በሃገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ የምንቆጠር መሆናችን ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት ''ሰላም፣ አንድነት እና ወንድማማችነታችንን የምናጠናክርበት ጊዜ ላይ እንገኛለን'' ብለዋል።

ከአንድ ቀን ቀደም ብለው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ የሚል መልእክት አስተላልፈዋል። '' ንብረቶችን በእሳት የሚያቃጥሉ በቴሌቪዥን መታየት ይችላሉ እኮ... በለበሱት ልብስ ልንለያቸውም እንችላለን።''

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ማለቱ በቀጥታ ሙስሊሞችን ነው የሚመለተከው፤ ስለሂጃባችንም ነው አስተያየቱን የሰጠው ትላለች ሪካት ሀሽሚ።

ሂጃብ ማድረግ የጀመርኩት በ16 ዓመቴ ቢሆንም አሁን ላይ የ 22 ዓመት ወጣት ሆኜ ግን ከምን ጊዜውም በበለጠ ስለሀይማኖቴ የሚነገረው የተሳሳተ አስተያየት ሰላም ይነሳኛል።

ማግለልን እንደ አማራጭ የሚወስዱ ፖሊሲዎችን ከመተቸት ወደኋላ አልልም። ነገር ግን ሁሌም ቢሆን ብሄራዊነትን የማልወድና ጸረ ሂንዱ ተደርጌ ነው የምቆጠረው።

ሀይማኖትና ብሄራዊነት በእጅጉ የተጣበቁበት አስቸጋሪና አስፈሪ ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው። አንዳንድ ጊዜ በመንገድ ላይ ሂጃብ ለብሼ ስሄድ ሰዎች በትኩረትና በመጠራጠር ሲመለከቱኝ አስተውላለሁ።

ሁሉንም አቅፋ የምትይዘውና እኔ የማውቃት ህንድ ይህች አይደለችም። 200 ሚሊየን የምንሆነው የህንድ ሙስሊሞች በፍርሀት እየኖርን ነው።