ለማግባት ሲሉ ለመገረዝ የተገደዱ ሱዳናውያን ሴቶች

ጥንዶች ሲደንሱ

የፎቶው ባለመብት, AFP

አንዳንድ ሱዳናዊያን ሴቶች ሰርጋቸው አንድ ወር ገደማ ሲቀረው ይገረዛሉ። ከዛ ቀደም የተገረዙ ቢሆንም እንኳን በድጋሚ ይገረዛሉ። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሴቶቹ ድንግል እንደሆኑ ማስመሰል ስላለባቸው ነው።

ሱዳን ውስጥ ከአራት እስከ አስር ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች ይገረዛሉ። በተለይም በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ሴቶች ሲገረዙ የብልታቸው ከንፈር ይቆረጣል፤ ብልታቸው እንዲጠብ ይሰፋል። ይህ ስፌት የሚለቀው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲፈጽሙ ነው።

87 በመቶ የሚደርሱ ከ14 እስከ 49 ዓመት የሚሆናቸው ሱዳናዊያን ሴቶች እንደተገረዙ የተባበሩት መንግሥታት ሰነድ ያሳያል።

አንዲት ልታገባ ያለች ሴት ከሰርጓ በፊት ልትገረዝ ከሆነ ብልቷ በድጋሚ እንዲሰፋ ይደረጋል።

የግርዛት አይነቶች

  • ክሊቶሪዲክቶሚይ (Clitoridectomy)፡ ይህ በቂንጥር እና በአካባቢው የሚገኝ ስስ ቆዳ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማስወገድ ነው።
  • ኤክሲሺን (Excision)፡ ይህ ቂንጥርን እና የብልትን የውስጠኛውን ከንፈር ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማስወገድ ነው።
  • ኢንፊቢዩሊሽን (Infibulation)፡ ይህ ቂንጥርን እና የብልት ክንፈሮችን ቆርጦ በመጣል ብልትን በመስፋት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ምቹ እንዳይሆን ማድረግ ነው።
  • ሌላኛው የግርዛት አይነት የሴት ልጅ የመራቢያ አካልን ማቃጠል፣ መብሳት፣ መቧጠጥ እና የመሳሰሉትን ያካትታል።

"ለቀናት መራመድ አልቻልኩም ነበር"

ማሀ (ለዚህ ታሪክ ሲባል ስሟ ተቀይሯል) የተገረዘችው ከሠርጓ ከሁለት ወር በፊት ነበር። ያገባችው ከእሷ በእድሜ በመጠኑ የሚበልጥ ሰው ነበር።

"በጣም ያም ነበር። እናቴ መገረዜን እንድታውቅ ስላልፈለግኩ እስካገግም ድረስ ለቀናት ከጓደኛዬ ጋር መቆየት ነበረብኝ፤ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ለመራመድ ተቸግሬ ነበር፤ መሽናትም ከብዶኝ ነበር።"

ማሀ እንደምትለው፤ ባለቤቷ ከጋብቻ በፊት ወሲብ እንደፈጸመች ቢያውቅ በእሷ ላይ እምነት አይጥልም።

"ከመጋባታችን በፊት ወሲብ እንደፈጸምኩ ካወቀ በእኔ ላይ እምነት ማሳደር ያቆማል፤ ከቤት እንዳልወጣ ሊያግደኝ፣ ስልኩን እንዳልጠቀም ሊከለክለኝም ይችላል።"

የዩኒቨርስቲ ምሩቋና በ20ዎቹ እድሜ ክልል የምትገኘው ማሀ ያደገችው ግርዛት በተከለከለበት ሰሜናዊ ሱዳን ሲሆን፤ የምትሠራውም ግርዛት ሕጋዊ በሆነባት በመዲናዋ ካርቱም ነው።

ማሀ ከሠርጓ በፊት በድብቅ በአዋላጅ ለመገረዝ ወደ ትውልድ ቀዬዋ ተመልሳ ነበር። ማሀና አዋላጇ ይተዋወቃሉ። አዋላጇ ማሀን በ5 ሺህ የሱዳን ፓውንድ (3,190 ብር ገደማ) ለመግረዝ ተስማሙ።

"የምገርዘው ብር ለማግኘት ነው"

በበርካታ ማኅበረሰቦች ባህል ሴቶች እስኪያገቡ ድንግል እንዲሆኑ ይጠበቃል። ሴቶች ሊያገቡ ሲሉ በቀዶ ህክምና ድንግል እንደሆኑ ለማስመሰል የሚገደዱትም ለዚሁ ነው።

ሀይመኖፕላስቲ "hymenoplasty" በመባል የሚታወቀው ቀዶ ህክምና ሱዳን ውስጥ አይሰጥም። አንድ ክሊኒክ ደግሞ ለባለትዳር ሴቶች ብቻ ቀዶ ህክምናውን ይሰጣል።

ሱዳናዊያን ሴቶች ብልታቸው ተሰፍቶ እንዲጠብ ከማድረግ ውጪ አማራጭ የላቸውም። አዋላጆቹ የሴቶችን የብልት ከንፈር ይቆርጣሉ፤ ሰፍተውም እንዲጠብ ያደርጋሉ።

ግርዛትን ለማስቆም የሚንቀሳቀሱት የማህጸን ሀኪም ዶ/ር ሳዋን ሰኢድ፤ "የሴት ልጅን የመራቢያ አካል መስፋትም ሆነ መብሳት ግርዛት ነው" ይላሉ።

የሱዳን የህክምና ባለሙያዎች ማኅበር ግርዛትን ስለከለከለ በካርቱም የሚገኙትን ጨምሮ በሌሎች ሆስፒታሎች ውስጥም ግርዛት አይካሄድም። ሲገርዙ የሚገኙ አዋላጆች ከሥራቸው ይባረራሉ፤ የህክምና መሣሪያቸውም ይወሰዳል።

ይህንን ጽሑፍ ያጠናቀረችው ጋዜጠኛ በጎበኘቻቸው ሦስት ሆስፒታሎች ውስጥ ያገኘቻቸው አዋላጆች ግን ሴቶችን ለመግረዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸውላታል።

ከአዋላጆቹ አንዷ ለጸሐፊዋ እንደነገረቻት፤ አንዳንዴ ሴቶችን የምትገርዘው ገንዘብ ለማግኘት ስትል ነው።

"በቅርቡ የ18 ዓመት ልጅ ገርዣለሁ (የኢንፊቢዩሊሽን ግርዛት)፤ ታዳጊዋ በአጎቷ ልጅ ተደፍራ ነበር። እናቷ እያለቀሱ ስለነበር ልርዳቸው ብዬ ገረዝኳት። በ'ሳሊም ኢኒሺየቲቭ' ሴቶችን ላለመግረዝ ቃል ብገባም፤ የልጅ ልጆቼን ለማሳደግ፣ የትምህርት ቤት ወጪያቸውን ለመሸፈን ገንዘብ ስለምፈልግ ገርዣታለሁ።"

'ሳሊም ኢኒሺየቲቭ'፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2008 ግርዛትን ለመግታት በተባበሩት መንግሥታት የተጀመረ ፕሮጀከት ነው።

ሱዳን ውስጥ በተለይም በወግ አጥባቂዎች ዘንድ ያለውን አመለካከት ለመቀየር ጊዜ ይወስዳል።

አንድ ካርቱም ውስጥ የሚኖር ግለሰብ "ለወደፊት የማገባት ሴት ድንግል እንድትሆን እፈልጋለሁ፤ ካልሆነች ግን ከእኔ ውጪ ከሌላ ሰው ጋር ወሲብ ትፈጽማለች ብዬ እጠረጥራታለሁ" ይላል።

ሱዳን ውስጥ ብዙ ወንዶች ከዚህ ግለሰቡ ጋር ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው። በርካታ ወንዶች ሴቶች "እንዲሰፉ" ይሻሉ።

ግርዛትን ለማስቆም ንቅናቄ እያደረጉ ያሉ የመብት ተሟጋቾች ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ ያደርጋሉ። ሴቶች ሱሪ እንዳይለብሱ ከመከልከል ባሻገር፤ በአደባባይ እንዴት መልበስና መንቀሳቀስ እንዳለባቸው፣ ከማን ጋር መነጋገር እንደሚችሉ እና ምን ሥራ መያዝ እንደሚፈቀድላቸው የሚደነግገው ሕግ ባለፈው ወር መሻሩ ደግሞ ተስፋቸውን የበለጠ አለምልሞታል።

ሕጉ 30 ዓመት በዘለቀው የኦማር አል-በሽር የአገዛዝ ዘመን የወጣ ነበር። ጥፋተኛ የተባሉ ሴቶች በግርፋት እና በድንጋይ ተወግረው ይቀጣሉ። ሊገደሉም ይችላሉ።

'አን ላን' የተባለው ግርዛትን ለማስቆም የሚሠራ ተቋም መስራች ናሂድ ቶዩባ እንደምትለው፤ ካለፉት ዘመናት በተሻለ አሁን ላይ ያሉ ሴቶች ግንዛቤ ጨምሯል።

"አሁን መንታ መንገድ ላይ ናቸው። በአንድ በኩል ግብረ ሥጋ ግንኙነት የማድረግ መብት እንደላቸው ያምናሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ብልታቸው ዳግመኛ እንዲሰፋ በማድረግና ሂጃብ በመልበስ ውሳኔያቸውን ይቀለብሳሉ።"

[ይህ ጽሑፍ በአፍሪካ ጋዜጠኞች የተጻፉ ደብዳቤዎች በሚስተናገዱበት "letters from African journalists" ለተባለው አምድ ከጋዜጠኛ ዘይነብ መሐመድ ሳላህ የተላከ ነው።]