አሜሪካ ዋካንዳን ከ'ሸሪኮቿ' ዝርዝር አወጣች

በፊልሙ ከተወኑት ሁለቱ

የፎቶው ባለመብት, MARVEL/DISNEY

የአሜሪካ መንግሥት የግብርና ክፍል፤ በ 'ብላክ ፓንተር' ፊልም ላይ ያለውን ልብ ወለዳዊ አገር 'ዋካንዳ' ነፃ የንግድ ሸሪኬ ብሎ በስህተት ሰይሞት የነበረ ቢሆንም፤ 'ዋካንዳ' ከዝርዝሩ መውጣቱ ተሰምቷል።

የአሜሪካ መንግሥት የ 'ዋካንዳ' ግዛትን ዝርዝሩ ውስጥ በስህተት ያስገባው በግብርና ክፍል የሠራተኞች ፈተና ወቅት ነበር።

የክፍሉ የዋጋ ቁጥጥር ዝርዝር ሲወጣ፤ 'ዋካንዳ' ን ከዳክዬ፣ ከአህያ እና ከላሞች ተርታ ወጥቶ ነበር።

'ዋካንዳ' በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ የሚኖር በጣም ኃይለኛ የሆነ ጥቁር ግስላ የሚኖርበት ልብ ወለዳዊ አገር ነው።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን ስለጉዳዩ ሲጠይቁ፤ ልብ ወለዳዊ አገሩ ከዝርዝሩ ተሰርዟል። "አሜሪካ የንግድ ጦርነት ጀምራለች" የሚሉ ሽሙጦችም ተሰምተዋል።

'ዋካንዳ' ለመጀመርያ ጊዜ የወጣው፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1966 'ፋንታስቲክ ፎር' የተሰኘ ፊልም ላይ ነበር። አምና ኦስካር ሽልማት ያሸነፈው 'ብላክ ፓንተር' ፊልም ላይ ሲነሳ ደግሞ ሁለተኛው ነው።

'ዋካንዳ' በስህተት ዝርዝር ውስጥ እንደገባ ያወቀው ፍራንሲስ ቴስንግ የተባለ ኒውዮርክ የሚኖር የሶፍትዌር መሃንዲሰ ነበር። ላመለከተው ስልጠና መርሃ ግብር የእቃዎች ዋጋ ዝርዝር በሚመለከትበት ግዜ ነበር 'ዋካንዳ' ን ዝርዝሩ ውስጥ ያየው።

ፍራንሲስ 'ዋካንዳ' ን ዝርዝሩ ውስጥ ሲያገኘው "በጣም እንደተደናገረ" ነበር ለሮይተርስ የተናገረው። "አገሩን ፊልሙ ላይ እንደማውቀው ረስቼው ከሌላ ነገር ጋ ተምታቶብኝ ነበር" ብሏል።

'ዋካንዳ' ከዝርዝሩ ውስጥ ከተሰረዘ በኋላ የአሜሪካ ግብርና ክፍል ቃል አቀባይ ለዋሽንግተን ፖስት እንዳሉት፤ 'ዋካንዳ' ሠራተኞችን ለመፈተን ሲባል ዝርዝር ውስጥ የገባ እንጂ በይፋ የተካተተ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

"ስለ ዋካንዳ የወጣው መረጃ ለመፈተን ከወጣ በኋላ መሰረዝ ነበረበት፤ አሁን ተሰርዟል" ብለዋል።

ልብ ወለዳዊ ስሞች በስህተት በገሀዱ ዓለም ሲመጡ ይህ ለመጀመርያ ግዜ አይደለም። በ2017 የፖላንድ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊቶልድ ዋዚስዝክዎስኪ ለሪፖርተሮች 'ቤሊዝ' እና ሳን 'ኤስኮበር' የተባሉ የሌሉ ስሞችን ተጠቅመው ተናግረው ነበር።