በግሪክ እናቱ ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ የጣለችው ጨቅላ በሕይወት ተገኘ

ቆሻሻ መጣያ

የፎቶው ባለመብት, Google street view

በግሪኳ ካላማታ ከተማ ቆሻሻ መጣያ ገንዳ ውስጥ አንድ ጨቅላ ልጅ መገኘቱን ተከትሎ የ24 ዓመት ሴት በቁጥጥር ሥር ዋለች።

ከተወለደ የቀናቶች ብቻ ዕድሜ እንዳለው የተገመተው ጨቅላ የተገኘው በአካባቢው የነበረች አንድ ሴት የልጁን ለቅሶ ከሰማች በኋላ ነበር።

ጨቅላው ሕይወቱ ሊተርፍ የቻለውም ቆሻሻ ገንዳውን የሚያነሳው መኪና በመዘግየቱ ነው።

የከተማዋ ከንቲባ ለጋዜጠኞች እንዳሉት፤ መኪናው በቦታው ቢደርስ ኖሮ ቆሻሻውን ስለሚጨፈልቀው ዘግናኝ ነገር ይከሰት ነበር።

ጨቅላው የተገኘው ከወረቀት የተሠራ ከረጢት ውስጥ፣ ጥልቅ በሆነው የቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ተጥሎ ነው።

ቫሲሊ ጾኒ የተባለችው ሴት ጨቅላውን ቆሻሻ መጣያ ውስጥ እንደተመለከተችው ከሰዎች እርዳታን ለማግኘት ድምጿን ከፍ አድርጋ ብትጮህም ማንም ለመርዳት ፍላጎት እንዳልነበረው ተናግራለች።

በአካባቢው የነበሩ ሰዎች "የሰማሽው የድመት ድምጽ እንጂ የሰው አይደለም" እንደሏት ለአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ቫሊሲ ተናግራለች።

ዘግይተውም ቢሆን በአከባቢው የተገኙት ሁለት የፖሊስ አባላት ጨቅላውን ታድገውታል።

ወደ ሆስፒታል የተወሰደው ጨቅላ እያገገመ እንደሚገኝ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላት የ24 ዓመቷ ሴት፤ የጨቅላው እናት መሆኗን እና የጣለችውም እሷ እንደሆነች አረጋግጧል።

የጆርጂያ ዜጋ ናት የተባለችው ይህች ሴት በግድያ ሙከራ ክስ ተመስርቶባታል።