የቻይና ልዑካን 'በፌደራል መንግሥት' ወደ ትግራይ እንዳይሄዱ ተከለከሉ

በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የትግራይ ክልል የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አብረሃም ተከስተ ከቻይና ልዑካን ጋር

የፎቶው ባለመብት, TIGRAY COMMUNICATION

የትግራይ ክልል በተደጋጋሚ እያጋጠመኝ ነው ባለው ችግር ሳቢያ ከፌደራል መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት "በጣም አሳሳቢ" አሳሳቢ ወደ ሆነ ደረጃ እደረሰ መምጣቱን የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ዶ/ር አብረሃም ተከስተ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ዶ/ር አብረሃምይህንን ያሉት ከትናንት በስቲያ ለሥራ ጉብኝት ወደ ትግራይ ክልል ጉዞ ሊያደርጉ የነበሩ የቻይና የሻንሺ ግዛት ልዑካን 'በፌደራል መንግሥት ትዕዛዝ' ወደ ትግራይ ክልል እንዳይጓዙ ተደርጓል ሲል የትግራይ ክልል መንግሥት ቅሬታውን ካሰማ በኋላ ነው።

በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የትግራይ ክልል የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አብረሃም ተከስተ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ በቁጥር ስድስት የሆኑት አባላቱ ከቻይን ወደ ኢትዮጵያ ከመጡባቸው ምክንያቶች አንዱ ከትግራይ ክልል ጋር በልማት እና አቅም ግንባታ ዙሪያ ለመተባባር የሚያስችል ስምምነት ለመፈራረም እና ጉብኝት ለማድረግ ነበረ።

ልዑካኑ ከትናንት በስቲያ ከፌደራል መንግሥት ጋር የነበራቸውን የሥራ ቆይታ አጠናቀው አመሻሹን ወደ መቀለ ለመብረር አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ ወደ ትግራይ መጓዝ እንደማይችሉ ከተነገራቸው በኋላ ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ስለመደረጉ መስማታቸውን ዶ/ር አብረሃም ይናገራሉ።

"የምቀበላቸው እኔ ነበርኩ። አውሮፕላኑ በሰዓቱ ቢያርፍም እንግዶቹን ይዞ አልመጣም" ይህንንም ተከትሎ ባደረጉት ማጣራት ''የሚያስፈልገውን ጨርሰው አውሮፕላን ውስጥ ከገቡ በኋላ መሄድ እንደማይችሉ እንደተነገራቸው ነው የሰማነው" ብለዋል ዶ/ር አብረሃም።

እንግዶቹ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይጓዙ የሚከለክል ምንም ምክንያት የለም ያሉት ዶ/ር አብረሃም፤ የግዛቷ አስተዳዳሪዎች ወደ ትግራይ እንዳይሄዱ መደረጋቸውን ''ተቀባይነት የሌለው ነው" ብለዋል።

ዶ/ር አብረሃም ከዚህ ቀደምም በፌደራል መንግሥት ባለሃብቶች እና የተቋማት ኃላፊዎች ወደ ትግራይ እንዳይጓዙ ጫና እንደሚደረግ ይናገራሉ።

"ወደ ትግራይ ሄዳችሁ ተብለው ማስፈራሪያ የሚደርስባቸው ምሁራን፣ ተቋማት፣ ባለሃብቶች እና የውጪ ሃገር ዜጎች አሉ። ይህንንም የዚያ አካል አድርጌ ነው የማየው" ብለዋል።

አክለውም "በትግራይ ህዝብ ላይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ይደረጋሉ። በትግራይ ህዝብ ላይም ውሸትም ጭምር በመጠቀም ሥነ-ልቦናዊ ጫና ለማሳደር ያልተደረገ ነገር የለም" ብለዋል።

ወደ ትግራይ ጉዞ ሊያደርጉ የነበረው የሻንሺ ግዛት ልዑክ በግዛቷ ምክትል አስተዳዳሪ የሚመራ መሆኑን አስታውሰው፤ ልዑካኑ ወደ መቀለ መሄድ ባለመቻላቸው እሳቸው አዲስ አበባ መጥተው በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በማዕድን እና ቱሪዝም መስኮች የመግባቢያ ሰነድ አዲስ አበባ ላይ መፈራረማቸውን ዶ/ር አብረሃም ገልፀዋል።

ዶ/ር አብረሃም በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት "በጣም አሳሳቢ" ሲሉ ይገለጹት ሲሆን፤ ግነኙነቱን ለማሻሻል የትግራይ ክልል ለመወያየት ሁልግዜም ቢሆን ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

"ሁኔታዎች በጣም እየተወሳሰቡ እየሄዱ ነው። የፌደራል መንግሥቱ ይህን ቆም ብሎ ማጤን አለበት። . . . እንደ ሃገር እንድንቆም ያስቻለን ሥርዓት አለ። ይህ ሥርዓት መከበር አለበት። ያጎደልነው ነገር ካለ መጠየቅ አለብን። ሌላውም እንደዛው" ብለዋል።

በትግራይ እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በወዳጅነት እና በመቀራረብ ለመፍታት ለምን እንደተሳነ ተጠይቀው "ከአንዳንዶቹ ጋር ጓደኝነታችን እንዳለ ነው። ስንገናኝ የልብ የልባችንን እናወጋለን ይሁን እንጂ መሰረታዊ የሆነ የፖለቲካ ልዩነት ተፈጥሯል" ብለዋል።

በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የክልሉ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር አብረሃም ተከስተ፤ ይህ የትግራይ ክልል እና የቻይናዋ ሻንሺ ግዛት ግንኙነት በኢትዮጵያ መንግሥት የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር አነሳሽነት የተጀመረ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርን ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ በስልክ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በተመሳሳይም ስለልዑካኑ ለማወቅ በኢትዮጵያ የቻይን ኤምባሲኒም ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ውጤት ሳያስገኝ ቀርቷል።