በወላይታ ሶዶ ከተማ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ግለሰቦች ተለቀቁ

የወላይታ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, WOLAITA ZONE CITY ADMINISTRATION FACEBOOK PAGE

የወላይታ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ካቀረበበት አንደኛ ዓመት ጋር በተያያዘ በነበረ እንቅስቃሴ ምክንያት በወላይታ ሶዶ ከተማ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ግለሰቦች መለቀቃቸው ተነገረ።

በጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ከነበሩት ሰዎች መካከልም የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ አንዱለም ታደሰ በስተቀር ሁሉም መለቀቃቸውን ቢቢሲ አረጋግጧል።

የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወሕዴግ) የወጣቶች ክንፍ አመራር አቶ አሸናፊ ከበደ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ዛሬ ማለዳ የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄው አንድ ዓመት መሙላቱን በማስመልከት ሰልፍ ለማካሄድ ከወጣቶች ጋር ተሰብስበው ባሉበት በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ተናግረዋል።

አቶ አሸናፊ እንደጠቀሱት ከእርሳቸው በተጨማሪ የወሕዴግ አባል የሆኑት አቶ ወርቅነህ ገበየሁም ሊያካሂዱት የነበረው ሰልፍ ያልተፈቀደ ነው በሚል መያዛቸውን ገልጸው፤ ከተያዙ በኋላም ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዳልተወሰዱ አስረድተዋል።

"ምንም ዓይነት የኤሌክትሮኒክስ ግንኙነት እንዳናደርግ ታግደን እንድንቆይ ከተደረግን በኋላ በመነጋገር ተለቀናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ነጋ አንጎሬ የወላይታ ሕዝብ የክልል ጥያቄ ዛሬ ታኅሣስ 10 ቀን 2012 ዓመት መሙላቱን በማስመልከት ሰልፍ ማድረጋቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የከተማው አስተዳደርም የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች የሀገር ሸማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ነጋዴዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚገኘው ጉተራ አዳራሽ ውይይት ማድረጋቸውን በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።

አቶ አሸናፊ የክልልነት ጥያቄያቸውን ካቀረቡ ዓመት እንደሞላቸው በማስታወስ "በሕጉ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ በደቡብ ክልል ስር አይደለንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ከማንኛውም እንቅስቃሴ ታቅባ ፀጥ ረጭ ያለች መሆኗን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በከተማዋ የትራንስፖርትም ሆነ የማኅበራዊ አገልግሎት አለመኖሩን የሚናገሩት ነዋሪዎች የመከላከያ ሠራዊት አባላት ግን በከፍተኛ ቁጥር ተሰማርተው እንደሚታዩ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በወላይታ ዞን ስር የሚገኙ የተለያዩ ከተሞች፤ ዞኑ በክልል የመደራጀቱን ጥያቄ በመደገፍ ሰልፍ ማድረጋቸውን አቶ አሸናፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ክንዶ ድዳዬ፣ ቦዲቲ፣ ቦሎሶ ቦምቤ፣ ሆብቻና አበላ አበያ ሰልፉ ከተደረገባቸው ከተሞች መካከል ይገኙበታል።

በወላይታ ዞኑ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ማብራሪያ ለማግኘት ቢቢሲ የዞኑ አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር በተደጋጋሚ ስልክ ቢደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም።